አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በቢሾፍቱ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ሥራ ሲጠናቀቅ የቱሪስት መስኅብነቷን በይበልጥ እንደሚጨምር የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት የሥራ መመሪያ መሠረት ከንቲባዋ በቢሾፍቱ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን መጎብኘታቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
ከጉብኝታቸው ጎንለጎንም ከከተማዋ አመራሮች፣ ከነዋሪ ተወካዮች ፣ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተያዙ እቅዶች እና በቅንጅት በሚሰራበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን ነው የገለጹት፡፡
የኮሪደር ልማቱ በከተማዋ በአምስት አካባቢዎች እየተከናወነ መሆኑን በመግለጽ÷ ይህም የመንገድ፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገድ፣ የሕዝብ መዝናኛ ፓርክ እና መንገዶችን የማስዋብ ተግባራትን እንደሚያካትት አመላክተዋል፡፡
እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ሥራ ሲጠናቀቅም በይበልጥ የቱሪስት መስኅብነቷን ይጨምራል፤ የከተማዋን የወደፊት ዕድልም ከፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡