አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የመፈጸም አቅምን በማጎልበት በአፍሪካ ተወዳዳሪ የኃይል ማዕከል ለመሆን እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
በተቋሙ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ ፍስሐ ጌታቸው እንዳሉት÷ በውጭ ተቋራጮች ይገነቡ የነበሩ የማከፋፈያ ጣቢያዎችና የማስተላለፊያ መስመሮች አሁን በተቋሙ የራስ አቅም እየተከናወኑ ነው፡፡
ለአብነትም የበቆጂ፣ የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞንና የደብረ ታቦር ማከፋፈያ ጣቢያዎች፣ የኦፕሬተር መኖሪያ ቤቶች፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ግንባታ እና የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ጥገና በራስ አቅም እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታም በተለያዩ ዘርፎች የተቋሙ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው ማለታቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገነኘው መረጃ አመላክቷል፡፡
ይህም ጥናትን መሠረት በማድረግ ጊዜና ገንዘብ በመቆጠብ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን ለማስፋፋት፣ የመልማት ጥያቄዎችን በዘላቂነት በመፍታት አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ለመስጠት አስችሏል ነው ያሉት፡፡
በማመንጫ፣ ማከፋፈያ ጣቢያዎችና ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ችግር ሲፈጠር ከውጭ ሀገር ባለሙያ እስከሚመጣ የሚከሰተውን የኃይል ብክነትና የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ማዳን መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
ተቋሙ የመፈጸም አቅምን በማሳደግ የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ለመሆን የያዘውን ራዕይ ለማሳካት ለሰው ኃይል ግንባታ ትኩረት መሥጠቱንም አንስተዋል፡፡