አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአንድ ሀገር ውስጥ ሀገራዊ ምክክርን ለማካሄድ እና ምክክሩም ፍሬያማ እንዲሆን መሟላት የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ።
ለእነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት የብዙ ባለድርሻ አካላት ሀላፊነት፣ እገዛና መልካም ፈቃድ በእጅጉ አስፈላጊ ነው።
ከዚህ ቀደም በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ያለፉ ሀገራትን ተሞክሮ በመመልከትና የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚከተሉት ሁኔታዎች ሀገራዊ ምክክርን ለማካሄድ እንደ ቅድመ ሁኔታ ይቀመጣሉ።
የዜጎች በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት አደጋ ላይ ከሆነ ሌሎች ነገሮችን ማሰብ ቅንጦት ይሆናል።
ስለሆነም ደም አፋሳሽ እና ህይወትን የሚያስከፍሉ ግጭቶች እና ተኩሶች መቆማቸው ለሀገራዊ ምክክሩ እንደ ቅድመ ሁኔታ ሊወሰድ የሚገባው መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡
ሀገራዊ ምክክር በባህሪው ዘለግ ያለ ጊዜን ከመውሰዱ እና በሂደቱም የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ከማሳተፉ አኳያ ከስሜታዊነት በፀዳ፣ በሰከነ መንፈስ፣ በመከባበርና በመደማመጥ ምክክርን ማድረግ ጠቃሚ ነው።
ሆኖም ግን ዜጎች በግጭት፣ በሠላም እጦት፣ በስነ-ልቦናዊ መረበሽ ውስጥ ብሎም በደህንነት ስጋት ውስጥ ካሉ የሀገራዊ ምክክር ሂደትን ማሳካት አዳጋች ይሆናል።
ሰላም ለሀገራዊ ምክክር ሂደት የመጀመሪያው እና ዋነኛ ቅድመ ሁኔታ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
በዜጎች መካከል ሊኖር የሚገባ የመከባበርና የመደማመጥ ባህል ለምክክር እጅግ አስፈላጊ ሲሆን÷ በኢትዮጵያ በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ቡድኖች፣ የሀሳብና የፖለቲካ መሪዎች መካከል መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ልዩነቶች እንዳሉ ይታወቃል።
በሀገራዊ ምክክር ሂደት የእነዚህ አካላት ተከባብሮና ተደማምጦ ለሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔን በጋራ ለማመንጨት ፈቃደኛ መሆን እጅግ ወሳኝ ነው።
በሀገራዊ ምክክር መሠረታዊ አስተምህሮት መሠረት ዜጎች ለምክከር ሲቀመጡ አንዱ የሌላውን ስብዕና በመቀበል እና በማመን መደማመጥ በመካከላቸው ሊኖር እንደሚገባ ይወሳል።
በመሆኑም በመከባበርና በመደማመጥ በምክክር ሂደት ለመሳተፍ ዝግጁ መሆን እንደ ሁለተኛ ቅድመ ሁኔታ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
ምክክር ለማድረግና ለሂደቱም ውጤታማነት እንደ ቅድመ ሁኔታ ሊቀመጥ የሚገባው ሶስተኛው ነገር ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት መኖሩና መረጋገጡ ነው።
ሀሳብን በነፃነት መግለፅ ከዲሞክራሲያዊ መብቶች አንዱ ሲሆን÷ በምክክር ሂደት ውስጥ የሀሳብ ብዘሀነት እንዲኖር መደላድል ይፈጥራል።
ከሀገራዊ ምክክር መሠረታዊ መርሆች አንዱ አካታችነት መሆኑ ሳይዘነጋ በዚህ ዓውድ ውስጥ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በባህል፣ በሀይማኖት፣ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በፆታ፣ በዕድሜ ወዘተ ከማሳተፍ በዘለለ የሀሳብ ልዩነቶችን ማስተናገድ የሀገራዊ ምክክሩ ቁልፍ ተግባር መሆኑም ሊዘነጋ አይገባም።
በመሆኑም ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ለአንድ ሀገር ሀገራዊ ምክክር ሂደት እጅግ መሰረታዊ እና እንደ ቁልፍ ቅድመ ሁኔታ ሊወሰድ ይችላል፡፡