የሀገር ውስጥ ዜና

አዲስ ዓመትን ስናከብር ለሰላምና እድገት በመስራት ሊሆን ይገባል- የሐይማኖት አባቶች

By Shambel Mihret

September 10, 2024

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መጪውን አዲስ ዓመት ስናከብር ለሀገር ሰላምና እድገት በመስራትና እርስ በርስ መረዳዳትን በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ የሐይማኖት አባቶች ገለጹ።

የሐይማኖት አባቶቹ አዲስ ዓመትን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት÷ አዕምሮን በማደስ በአዲሱ አመት ኢትዮጵያን እናድስ ብለዋል፡፡

በአዲሱ ዘመን አለመግባባትን በዕርቅ ፈትተን በመታደስ ማህበረሰብን ለመገንባት ጥረት ማድረግ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የተለያዩ የሐይማኖቶች ተከታዮች በሰላምና በፍቅር ተቻችለውና ተከባብረው የሚኖሩባት አገር መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡

ሁሉም ይህንን ተቻችሎ የመኖር ልምዱን አጠናክሮ መቀጥል እንደሚገባው በመግለጽ በአዲሱ ዓመት እርቅና ሰላም በማውረድ ለሀገር ልማትና ዕድገት መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ የሱስም÷በአዲሱ ዓመት ለለውጥ መዘጋጀት ያስፈልጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

አዲሱን ዓመት ለሀገር ሰላምና እድገት የምንሰራበትና የተቸገሩትን የምናግዝበት የአንድነት፣ የይቅርታና የምህረት ሰላም የሰፈነበት ዘመን እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ÷ አዲሱ ዘመን ከቤተሰብ አንስቶ በሀገር ደረጃ ለሰላም የምንጸልይበትና የምንተገብርበት ዘመን እንዲሆን ተመኝተዋል።

በአዲሱ ዓመት እርስ በርስ በመከባበርና በትጋት በመስራት ሰላም እንዲሰፍን መንፈሳዊና ሀገራዊ ኃላፊነትን መወጣት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡