Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አዲሱ ዓመት በአዲስ አስተሳሰብ የተጀመሩ ልማቶች የሚጎለብቱበት ሊሆን ይገባል – አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲሱ ዓመት በአዲስ መነሳሳትና አስተሳሰብ የተጀመሩ ልማቶች ተጠናክረው የሚቀጥሉበት ሊሆን እንደሚገባ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ለአዲስ አመት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ዓመቱ የሰላም፣ የጤናና የስኬት እንዲሁም መቻቻል፣ መከባበርና መፈቃቀድ የሰፈነበት እንዲሆን ተመኝተዋል።

ሰላም ካለ የትኛውንም እቅድና ዓላማ ማሳካት እንደሚቻል ጠቅሰው፥ ህዝቡ ከፀጥታ ተቋማት ጎን በመሆን የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ለተጀመሩ የልማት ስራዎች ዘላቂነት የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ ያላት ሀገር ናት በማለት ገልጸው፥ አዲሱ ዓመት በኢኮኖሚና ልማት እንዲሁም በተለያዩ መስኮች የተመዘገቡ ውጤቶች ተጠናክረው የሚቀጥሉበት ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተለይ በዓሉን ስናከብር የአብሮነትና በጎነት መንፈስን በማፅናት አቅመ ደካሞችና ጠያቂ የሌላቸውን ወገኖች በመጠየቅ ያለንን በማካፈል እርስ በእርስ በመረዳዳት ሊሆን ይገባል ማለታቸውን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።

Exit mobile version