Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

2017 የብዙ ችግሮቻችን መዝጊያ፤ የብዙ ጅምሮቻችን መፍኪያ ይሆናል – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 2017 የብዙ ችግሮቻችን መዝጊያ፤ የብዙ ጅምሮቻችን መፍኪያ ይሆናል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የአዲስ ዓመት መልዕክታቸው አስተላለፉ፡፡

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:-

ውድ ኢትዮጵያውያን

የበዓሉ ድባብ እንደ ማንም ኢትዮጵያዊ ራሴን ወደ ኋላ ይወስደኛል፡፡ ከልጅነት እስከ ዕውቀት የከወንናቸው የዘመን መለወጫ ትዝታዎች በዓይነ ኅሊናዬ መጡ፡፡ ያኔ በልጅነት ጊዜ የኢትዮጵያ ልዩ መገለጫ የሆኑትን የጳጉሜ ቀናትን በማለዳ ወፍ ሳይጮህ በወንዞቻችን ፏፏቴ ሥር ሄደን እንጠመቅ ነበር፡፡ በአካልም በመንፈስም ጸድተን አዲሱን ዓመት ለመቀበል እንሯሯጥ ነበር፡፡

ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት

ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት፤ ይባል ስለነበር የልጅነት ዝግጅታችን ከዚያ ይጀምራል፡፡

መስከረም የሚለው ስም ከመክረም ከመሰንበት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ወንዙ አላሻግር ብሎት የከረመው ዘመድ ወዳጅ ሁሉ በመስከረም በዓላት ይገናኛል፡፡ ክረምት የሚለው ስያሜ ራሱ ከመክረምና ከመሰንበት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ “እንደምን ከረምክ” እንደምንለው፡፡

አዲስ ዓመት መምጣቱን የዘመን መቁጠሪያው ባይነግረን እንኳን የጋራ ሸንተረሩ መለወጥ፤ የአዳዲስ አዕዋፍን መምጣት፣ የአደይ አበባ ፍካት፣ የመዓዛው መታወድ፣ የልጃገረዶች ውብ ዜማ እና የአበው ምርቃት ይነግረናል፡፡ ልጆች ሆነን እነዚያን አበቦች ለመሰብሰብ፣ በወንዞቹ ለመራጨት፣ ከአዕዋፉ ጋር ለመዝለል እና ጅራፍ ለማጮህ የወጣንበትና የወረድንበት ቦታ ሁሉ ትዝ ይለኛል፡፡ ከምንም በላይ አዲስ ዓመት ዋዜማው፣ ዕለቱና ማግሥቱ ለልጆች የተፈጠረ ሁሉ ይመስለኛል፡፡

ዛሬም በቤተሰብ ያለን ሚና እና ኃላፊነት ቢለወጥም – ጊዜው፣ ቦታው እና ሁኔታው ሁሉ በሚፈቅደው መጠን ከእማት እና ከአበው የወረስነውን በዓልና ባህል በክብር እያስቀጠልን እንደሆንን አምናለሁ፡፡ ዘመን አልፎ ዘመን ቢተካም የዘመን መለወጫ በዓል ዘመን የማይሽረው የኢትዮጵያ እና የሕዝቦቿ የማንነታቸው መገለጫ ልዩ ስጦታ ሆኖ ይኸው ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡

ውድ ኢትዮጵያውያን

አዲስ ዓመት ሲመጣ የአብሮነት፣ የጸሎት፣ የተስፋ እና የመልካም ነገሮች ምኞት ወቅት ነው፡፡ ዛሬም በዋዜማው ለሕዝባችን፣ ለሀገራችን እንዲሁም ለመላው ዓለም ሁሉ መልካሙን የሚሆንበት ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡

የዘመን መለወጥ ከልብና ከሥራ ለውጥ ጋር ካልተያያዘ የእድሜ ጭማሬ ብቻ ሆኖ ያልፋል፡፡ ያውም እድሜ ከጨመረ ነው፡፡ እድሜ እንደ በጀት ከታየ እየተቀነሰ እንጂ እየጨመረ ሊሄድ አይችልም፡፡ ለዚህ ነው ጊዜ የለንም በሚል ስሜት እንሥራ የምንለው፡፡ በ2016 እና በ2017 መካከል ለውጡ የ6 ቁጥርና የ7 ቁጥር ብቻ ከሆነ ዘመን ተለወጠልን ከማለት ዘመን ተለወጠብን ማለት ይሻላል፡፡

የዛሬዋ ቀን የመጨረሻ የግምገማ ቀናችን መሆን አለባት፡፡ ዓመቱን ምን ሠርተን ጨረስነው? ከ2015 ምን የተለየ ለውጥ አመጣን? በ2016 ለኢትዮጵያ ምን አዲስ ዕሴት ጨመርንላት? ለኢትዮጵያ ዕሴት ሆንን ወይስ ዕዳ? ይሄን ሳይመረምሩ ዘመን ተለወጠ ማለት እንዴት ይቻላል?
ለምሳሌ አዲስ አበባ አዲሱን ዓመት አዲስ ሆና ነው የተቀበለችው? የ2015 እና የ2016 አዲስ አበባ ይለያያሉ፡፡ በየሕይወታችንና በየተቋማችን 2015 እና 2016 እንደ አዲስ አበባ ከተለያዩ 2017 በጉጉት የሚጠበቅ ዓመት ይሆናል፡፡

ሕዳሴ ግድቡን አገባድደን፤ አረንጓዴ ዐሻራን አሳክተን፤ ስንዴን በሀገር ውስጥ ተክተን፤ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶችን አሳክተን፤ ትልቁን የዓባይ ድልድይ አጠናቅቀን፤ ሀገራዊ ምክክርን ጀምረን፤ ጦርነትን በሰላም ስምምነት አብርደን፤ ተፈናቃዮችን መመለስ ጀምረን፤ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን መተግበር ጀምረን፤ የምንሰናበተው ዓመት ነው – 2016፤አምናለሁ፤ 2017 የብዙ ችግሮቻችን መዝጊያ፤ የብዙ ጅምሮቻችን መፍኪያ ይሆናል፡፡ ሐሳቦቻችን ሥር ይይዛሉ፤ መርሖቻችን መሬት ይረግጣሉ፤ ውጤቶቻችን በገሐድ ይታያሉ፤ድክመቶቻችን ይታረማሉ፤ ታላላቅ ፕሮጀክቶቻችን ይጠናቀቃሉ፡፡

ውድ ኢትዮጵያውያን

እነሆ ከፊታችን 365 ገጾች ያሉት አንድ ትልቅ መዝገብ ተከፍቷል፡፡ ምንም አልተጻፈበትም፡፡ በዚህ መዝገብ ላይ የኢትዮጵያን ብልጽግና እንጻፍበት፡፡ እኛ የኢትዮጵያን ብልጽግና ካልጻፍንበት ሌሎች የኢትዮጵያን ድካም ይጽፉበታል፡፡ መሽቀዳደም አለብን፡፡ እሽቅድድሙ ከጊዜ ጋር ነው፡፡ ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ጋር ነው፡፡

በመጨረሻም አዲሱ ዓመት የጀመርናቸውን ውጥን ሥራዎች ፍሬዎችን የምናይበት፣ አዳዲስ የከፍታ ሐሳቦቻችንን ለማሳካት የተግባር ዘሮችን የምንዘራበት፤ በትጋት እና በቁርጠኝነት ለሕዝባችን የገባነውን ቃል የምንፈጽምበት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡

መልካም አዲስ ዓመት

Exit mobile version