አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ የአዲስ አመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የመግለጫው ሙሉ ቃል ከዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል:-
ለመላው ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንኳን ከአመት አመት አሸጋገራችሁ
እንኳን ለአዲሱ 2017 አመት በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን! አዲሱ አመት የሰላም የብልጽግና የመተሳሰብ እና በህብረት የማደግ አመት እንዲሆንልን መልካም ምኞቴን በቅድሚያ እገልጻለሁ፡፡
ጊዜ ከፈጣሪ ለሁላችንም የተሰጠን ታላቅ ሀብታችን ነው፡፡ ጊዜ ህይወታችን ነው፤ ዕድሜያችን የጊዚያት ድምር ውጤት ነው፡፡ የተቸረንን ዕድሜያችን በአመታት ተከፋፍለው በህይወት ዘመናችን ራሳችንንና ሌሎችን የሚጠቅሙ ቁምነገሮችን እንድንሰራ ይጠበቃል፡፡
እነሆ እንደኛ እንደ ኢትዮጵያውን አቆጣጠር 2016 አመትን ሸኝተን 2017 አዲሱ አመትን በአዲስ ተስፋ በአዲስ መነሳሳት አርሂብ ብለን በክብር ተቀብለናል፡፡ ከአመት አመት መድረስ በፈጣሪ የሚሰጥ ችሮታ ነውና ለአምላካችን ታላቅ ምስጋናን በማቅረብ አዲሱን አመት እንዲባርክልን እንለምነዋለን፡፡
2016 አመት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የብልጽግና ማማ ከፍ ለማድረግ እንደ ክልላችንም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ህብረ ብሔራዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት ላይ የተመሠረተ ሀገረ መንግስት ግንባታ፤ በወንድማማችነት እሴት ላይ የቆመ ህረ ብሄራዊ አንድነት ግንባታ፤ ብዝሀ ልሳን የሆነ የፖለቲካ ማህረሰብ ግንባታ፤ ብሄራዊ መግባባት እና እርቅን በመጠቀም ዘላቂ ሰላም ግንባታ ረገድ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል።
ከምግብ ዋስትና ጥያቄ የተሻገረ የዜጎች የምርጫ አድማስ የሚያሰፋ የበለጸገ ኢኮኖሚ መገንባት፤ የዜጎች የስራ ዕድልና ተጠቃሚነት መብት ማረጋገጥ፤ የኑሮ ውድነት ማረጋጋትና መቆጣጠር፤ አካታችና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያረጋግጥ የብብሀ ዘር ኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ መከተል፤የአረንጓዴ አሻራ ስራን በማጠናር አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት፤ ጥራቱን የጠበቀ ፍትሀዊ የመሰረተ ልማት ስርጭት ማረጋጥ፤ ፍትሀዊና ጥራት ያላቸው መሰረተ ልማት መዘርጋት፤ ለቀጣዩ ትውልድ ዕዳን የማያወርስ ዘላቂ የልማት ፋይናንስ ማረጋገጥ፤ የህዝባችንን ፍላጎት የሚያሟላ ፍትሐዊ የማበህራዊ አገልግሎት ስርዓት መዘርጋት እና ተያያዥ ጉዳዮችም ተከናውነዋል።
በአዲሱ 2017 አመትም የተሻለ ስራ ለመስራት እንደ መንግስት በፖለቲካዊ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚ ዘርፎች ኢላማዎች ተቀምጠው ለተፈጻሚነቱ ርብርብ የሚደረግ ይሆናል፡፡ ሁሌም ቢሆን ዕድገትና ብልጽግና ሁለንተናዊ መሆን ስለሚገባው በሁሉም አካባቢዎችና ዘርፎች የሚጠበቀውን ውጤት ለማስመዝገብ እጅ ለእጅ ተያይዘን አዲሱ አመትን ለነገው ትውልድ አሻራ አስቀምጠን ማለፍ የምንችልበት እንዲሆን ጥሪዬን አቀርባለሁ።
ለሁሉም ነገር መሰረቱ ከአእምሯችንና ከውስጣችን የሚጀምር በመሆኑ ሁላችንም ራሳችንን ለለውጥና ለእድገት ዝግጁ በማድረግ ለሀገሬ ምን አደረግኩ? ብለን በመጠየቅ ለቀጣይ ትውልድ ማውረስ የምንችለውን ግዴታ በመወጣት ሀላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል።
በአዲሱ አመት በአዲስ መንፈስ በአዲስ መነሳሳት ለኢትዮጵያችን ከፍታና ለብልጽግናችን የራሳችንን አሻራ እንድናኖር ጥሪዬን እያቀረብኩኝ በድጋሜ እንኳን አደረሳቹህ አደረሰን እላለሁ።