የሀገር ውስጥ ዜና

በቀጣዮቹ 10 ቀናት ዝናብ ሰጪ ገጽታዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ቀጣይነት ይኖራቸዋል

By Melaku Gedif

September 10, 2024

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀጣዮቹ አስር ቀናት ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎችላይ ቀጣይነት እንደሚኖራቸው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

በመደበኛ ሁኔታ በአሥሩ ቀናት የክረምት ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ከሰሜንና ከሰሜን ምሥራቅ አካባቢዎች የሚዳከሙ ሲሆን ፥ በዚህም የወቅቱ ዝናብ በመጠንም ሆነ በሥርጭት እየቀነሰ እንደሚሄድ ተጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል የክረምት ዝናብ ድንበር ወደ ምዕራባዊው አጋማሽና ወደ ደቡባዊው የኢትዮጵያ ክፍሎች ስለሚያፈገፍግ ዝናቡ በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ ቀጣይነት እንደሚኖረው ተመላክቷል፡፡

በተመሳሳይ የደቡብ የሀገሪቱ ሥፍራዎች 2ኛውን የዝናብ ወቅታቸውን ቀስ በቀስ ማግኘት የሚጀምሩ ሲሆን÷ዝናብ ሰጭ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ቀጣይነት ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡

በመሆኑም በሰሜን ምዕራብ፣ በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ እንዲሁም በመካከለኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በፀሃይ ሃይል ታግዞ ከሚጠናከሩ የደመና ክምችቶች ጋር ተያይዞ በአንዳንድ ስፍራዎች ላይ አልፎ አልፎ ከባድ ዝናብ እንደሚኖር አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩ የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

በተጨማሪም በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አከባቢዎች ከቀን ወደ ቀን የደመና ሽፋን እየጨመረ የሚሄድ ሲሆን ፥ በዚህም ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ፡፡

በአጠቃላይ በሚቀጥሉት አስር ቀናት ከትግራይ ክልል የማዕከላዊ፣ የሰሜን ምዕራብ እና የምዕራብ ዞኖች፤ ከአማራ ክልል ሰሜን፣ ምዕራብ፣ ማዕከላዊ እና ደቡብ ጎንደር፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ጎጃም፣ አዊ፣ ሰሜን ሸዋ፣ እና የኦሮሞ ብሄረሰብ ልዩ ዞን ዞኖች፤ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል፣ አሶሳ፣ ካማሺ እና የማኦኮሞ ልዩ ዞን፤ ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ፣ ሆሮጉዱሩ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ቡኖ በደሌ፣ ኢሉባቦር፣ ጅማ፣ አርሲ እና ምዕራብ አርስ፤ ምስራቅ፣ ምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ሰሜን ሸዋ (ሰላሌ)፣ አዲስ አበባ፤ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ፣ ጉራጌ እና ምስራቅ ጉራጌ፣ የቀበና፣ የጠምባሮ እና የማረቆ ልዩ ወረዳ፣ ሀላባ፣ ሀዲያ እንዲሁም የየም ልዩ ዞን፤ ሁሉም የሲዳማ ክልል ዞኖች ላይ በብዙ ቦታዎቻቸው ላይ ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል ከሚጠናከሩት የአየር ሁኔታ ክስተቶች ላይ በመነሳት ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ እና ምዕራብ ሀረርጌ፣ ባሌ እና ምስራቅ ባሌ፣ ቦረና፣ ጉጂ ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ ከአፋር ክልል ፋንቲ፣ ማሂ፣ ሃሪ እና ጋቢ፣ ዞኖች፤ከአማራ ክልል ሰሜን እና ደቡብ ወሎ፣ ዋህግምራ ዞኖች፤ ከትግራይ የደቡብ እና የደቡብ ምስራቅ ዞኖች፤ክልል ከጋምቤላ ክልል የኢታንግ ልዩ ዞን፣ ኑዌር፣ አኝዋክ እና ማዣንግ ዞኖች፤ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ፣ ጎፋ፣ ጌዲኦ እና ወላይታ፣ ኮንሶ፣ አማሮ፣ ባስኬቶ፣ ቡርጂ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች ዞኖች፤ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ቤንች ሸኮ፣ ዳውሮ፣ ከፋ፣ ሸካ፣ ኮንታ እና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች፤ ከሱማሌ ክልል ሲቲ፣ ፋፋን፣ ኤረር፣ ጀረር፣ ኖጎብ፣ ሊበን እና ዳዋ ዞኖች፤ እንዲሁም ሀረሪ እና ድሬዳዋ ላይ ቀላል መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተጠቅሷል፡