የሀገር ውስጥ ዜና

‹‹የነገው ትውልድ እጣ ፈንታ በብልፅግና ጉዟችን ውስጥ ምን ሊሆን እንደሚችል በፖሊሲዎቻችን እና በፍኖተ ብልጽግና እቅዳችን ላይ በግልፅ አስቀምጠናል።

By ዮሐንስ ደርበው

September 10, 2024

የነገው ትውልድ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል በፍኖተ ብልጽግና እቅዳችን ላይ በግልፅ አስቀምጠናል – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የነገው ትውልድ እጣ ፈንታ በብልፅግና ጉዟችን ውስጥ ምን ሊሆን እንደሚችል በፖሊሲዎቻችን እና በፍኖተ ብልጽግና እቅዳችን ላይ በግልፅ አስቀምጠናል ሲሉ በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለፁ።

አቶ አደም ፋራህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው÷ በስነ ምግባር የታነፀ፣ ተስፋው ሙሉ እንደሆነ የሚያምን፣ ለወንድማማችነት እና እህትማማችነት ቦታ የሚሰጥ፣ የሰብዓዊነት አስተሳሰቡ የዳበረ፣ የሞራል ልዕልናው በልህቀት የተሞላ ትውልድ ኢትዮጵያ በቀጣይነት ይኖራት ዘንድ ታላቅ ህልምን በማንገብ ጉዟችንን ጀምረናል ብለዋል፡፡

ይህም እውን ይሆን ዘንድ የትምህርት፣ የጤና፣ የከተማ ልማትና ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎቻችን የነገውን ትውልድ ታሳቢ በማድረግ እንዲሻሻሉ እንዲሁም በአዳዲስ ሀሳቦች የቀጣዩን ትውልድ ዘመን እንዲዋጁ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

ለቴክኖሎጂ፣ ለዘመናዊነት፣ ለፈጠራ ሀሳቦች ቅርብ የሆነ በሀገር በቀል እሳቤዎች ተመርኩዞ ማህበረሰባዊ እድገትን የሚያረጋግጥ ትውልድን ለመቅረፅ የጀመርናቸው ስራዎችም በአጭር ጊዜ ውስጥ ፍሬ ማፍራት ጀምረዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ጳጉሜን 5 የነገ ቀን የመደመር ትውልድ በሚል ስያሜ የተሰጠው ባለ ተስፋው ትውልድ ይበልጥ ሀገሩን እንዲወድ፣ በሀገሩ ተስፋ እንዳለው እንዲያስብ መሆኑን ገልጸዋል።

ለትውልዱ አለንልህ ብለን ከጎኑ የምንቆምበት፣ ከስህተቶቻችን ተምረን ነገን ውብ አድርገን የተሻለች ሀገር እንደምናስረክበው ቃል የምንገባበት ነውና እንኳን አደረሳችሁ እንኳን አደረሰን ለማለት እወዳለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡