አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በጫና ውስጥ ሆነው ነገን ዛሬ የገነቡበት የጋራ ትጋት ውጤት መሆኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ክፍሌ ሆሮ (ኢ/ር) ገለጹ።
ፕሮጀክቱ ፈተናዎችን አልፎ የመጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ መድረሱን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ÷ ኢትዮጵያውያንም የጋራ ሃብታቸውና የአንድነታቸው አርማ ለሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያውያን የኅብረት ተምሳሌት የሆነው ግድቡ አጠቃላይ የግንባታ ሂደት 96 ነጥብ 8 በመቶ ተጠናቅቋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ፕሮጀክቱ ከለውጡ በፊት በነበሩ የፖለቲካ ውሳኔዎች ፈተና ተጋርጦበት እንደነበር አስታውሰው፥ ለውጡ መንግሥት በፍጥነት የወሰዳቸው ርምጃዎች ለፕሮጀክቱ ዳግም ሕይወት መዝራታቸውን አስረድተዋል፡፡
ግንባታውን አሁነ የሚገኝበት ደረጃ ለማድረስ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል ብለዋል።
የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በጫና ውስጥ ሆነው ነገን ዛሬ የገነቡበት የጋራ ትጋት ውጤት መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡