አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዋሬ መንደር ላይ የታየው ለውጥ ለዜጎች ምቹ ሀገር የመገንባትና አካታች ልማትን እውን የማድረግ ምሳሌ መሆኑን ሚኒስትሮች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከቀናት በፊት በአዋሬ መንደር የተገነቡ 275 ቤቶችን ቁልፍ ለነዋሪዎች ማስረከባቸው ይታወቃል።
መኖሪያ ቤቶቹም በክረምት በጎ ፈቃድ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተገነቡ ሲሆን÷ አረንጓዴ ሥፍራዎች፣ የልጆች መጫዎቻ ሥፍራዎች እንዲሁም የመኪና መቆሚያን አካትተዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እንዳሉት÷ ምቹ መንደር የማኅበረሰብ ለውጥ የሚያመጣና ሀገር የሚቀየርበት እንዲሁም ከጤና አንፃር ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው።
መንደሩ ለሕፃናት አዕምሮ እድገትና ለእናቶች ጤንነት ጉልህ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።
የአዋሬ መንደር አረንጓዴ አካባቢን በውስጡ የያዘ መሆኑ ኅብረተሰቡ ንፁህ አየር እንዲተነፍስና ራሱን ከበሽታዎች ለመጠበቅና ለመከላከል ሚና እንዳለው አስረድተዋል
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ከለውጡ ወዲህ የሚከናወኑ ተግባራት ሰው ተኮርና ማኅበራዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የአዋሬ መንደር ከዚህ ቀደም ለኑሮ የማይመች እንደነበር አንስተው÷ አዲስ የተገነባው መንደር አቅመ ደካሞችን ያካተተ ልማትን በመተግበር ከተማና ሀገርን መቀየር እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል።
የአዋሬ መንደር ለሁሉም በሚመች መልኩ አካታች ሆኖ የተገነባ በመሆኑ ለማኅበራዊ ጥበቃና ዜጎች ተጠቃሚነት አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን ለኢዜአ ብራርተዋል።
ጎስቋላ የነበረው የአዋሬ መንደር ዛሬ ላይ ለነዋሪዎች ምቹ ወደሆነ አካባቢ መቀየሩን የተናገሩት ደግሞ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ናቸው።
በአዋሬ መንደር የታዩ ተምሳሌታዊ ተግባራትን በሌሎች አካባቢዎችም በማስቀጠል የተሻለች ሀገርን ለማየት መትጋት እንደሚገባ የሚያስተምሩ ስለመሆናቸውም ጠቁመዋል።