Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ማዕከሉ ማንኛውንም ግዳጅ በብቃት መወጣት የሚያስችለውን አቅም ማጎልበቱን ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመከላከያ ሜካናይዝድ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ወቅቱ የሚያስፈልገውን ዝግጁነት ያሟላና ማንኛውንም ግዳጅ በብቃት መወጣት የሚያስችለውን አቅም ማጎልበቱን አስታውቋል፡፡

የሜካናይዝድ ዕዙ ማሰልጠኛ የስልጠና ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት እና የአዲስ ዓመት አቀባበል መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡

በመርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት የሜካናይዝድ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ዋና አዛዥ ሜ/ጀ ከፍያለው አምዴ÷የተሰጠንን ከባድ ተልዕኮ ለመወጣት የስልጠና ማዕከሉ ሁሌም በትጋት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከ74 ዓመት በፊት የሜካናይዝድ ጦር መኖር አስፈላጊነትን ተረድቶ ሜካናይዝድ መመስረቱን አንስተው÷ማዕከሉ ዛሬ ላይ ጠላትን በአስተማማኝ ሁኔታ መመከት የሚያስችል አቅም እንዲገነባ ማስቻሉን ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷን በአግባቡ ተጠቅማ እንዳትለማና እንዳትበለፅግ የሚፈልጉ ሃይሎች በተለያ ጊዜያት በሃይል ለመውረር ሞክረው በተባበረ ክንድ አላማቸው እንዳይሳካ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

ዛሬም የኢትዮጵያን የውስጥ ችግር በማየትና በሌሎች የተሳሳቱ ግምቶች ትንኮሳዎችን እያደረጉ መሆኑን ጠቁመው÷ ሰራዊቱ ማንኛውንም ትንኮሳ ለመመከት በአስተማማኝ ቁመናና ብቃት ላይ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል፡፡

በሜካናይዝድ ዕዙ የማስልጠኛ ማዕከሉ ዋና አዛዥ ኮሎኔል አየለ ወ/ጊዮርጊስ በበኩላቸው ÷ የሁሉም ሜካናይዝድ ክፍለጦር ሙያተኞች የሰራዊቱን የማድረግ አቅም ከማሳደግ ባለፈ ዘመኑ የደረሰበትን የስልጠና አቅምና ቴክኖሎጂ ሰራዊቱ እንዲጨብጥ ያደርጋሉ ብለዋል።

መከላከያ ሰራዊት ለሁሉም የኢትዮጵያ ዜጎች አስተማማኝ ጋሻ መሆኑን ገልጸው÷ሰራዊቱ ድሮም፣ ዛሬም ወደፊትም ለሀገሩ የሕይወት ዋጋ እየከፈለ ይቀጥላል ሲሉ አውስተዋል፡፡

በዓለምሰገድ አሳዬ

Exit mobile version