ቢዝነስ

የኢሬቻ በዓልን ከኢኮኖሚያዊ ትሩፋቱ ጋር በማስተሳሰር ማክበር እንደሚገባ ተመላከተ

By Melaku Gedif

September 09, 2024

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢሬቻ በዓን ባህላዊ እሴቱን ከኢኮኖሚያዊ ትሩፋቱ ጋር በማስተሳሰር ማክበር እንደሚገባ የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፡፡

ኢሬቻ ኤክስፖ 2017 ከፊታችን መስከረም 20 እስከ 24 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

የኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ህዝብ ምድርና ሰማይን ለፈጠረው እና ከዘመን ወደ ዘመን በሰላም ላሸጋገረው አምላክ ምስጋና የሚያቀርብበት በዓል ነው፡፡

የኢሬቻ በዓል አከባበር በየዓመቱ እየጎለበተ፣እያማረ እየደመቀ የመጣ ሲሆን÷የኦሮሞን ባህላዊ እሴቶች በማስተዋወቅ ረገድ ታላቅ እምርታ እያሳየ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም በቀጣይ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል ከኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ጠቀሜታው ጋር በማስተሳሰር ለማክበር ዝግጅት መደረጉ ተገልጿል፡፡

በዚህ መሰረትም የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከሀገሬ ኢቨንትስና ፕሮሞሽን ጋር በመተባበር ከፊታችን መስከረም 20 እስከ 24 ቀን 2017 ዓ.ም የሚካሄድ “ኢሬቻ ኤክስፖ 2017” የተሰኘ ኤክስፖ ማዘጋጀታቸው ተጠቁሟል፡፡

በኤክስፖው የኦሮሞን ባህላዊ ትውፊት የሚያንጸባርቁ፣ አልባሳት፣ የምግብ አይነቶች፣ ቅርሶች እና ውዝዋዜዎችእና ሌሎች በህላዊ ክዋኔዎችእንደሚቀርቡ ተጠቅሷል፡፡

ኤክስፖው ባዛር፣ ዐውደ ርዕይ፣ ፓናል ውይይት፣ ኮንሰርት እና ሌሎች መርሐ ግብሮችን እንደሚያካትት የተገለጸ ሲሆን÷ የተለያዩ የንግድ ዘርፎች የተሰማሩ ድርጅቶች ምርትና አገልግሎቶቻቸውን እንደሚያቀርቡም ተጠቁሟል፡፡