አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰላም የሰፈነባት ጠንካራ፣ ሉዓላዊነቷና ብልጽግናዋ የተረጋገጠ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባት የምንችለው በህብር ነው ሲሉ በምክትል ጠ/ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
የፓርቲው ዋና ጽ/ቤት አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ከ150 በላይ ለሚሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ አድርጓል፡፡
አቶ አደም ፋራህ፥ ፓርቲያችን ባለፉት ዓመታት ያስመዘባቸው ድሎች የሕብረ ውጤቶች ናቸው ብለዋል፡፡
ህብር ለኢትዮጵያ እውነትም መልክም ነው፤ በኢትዮጵያ የአስተሳሰብ፣ የብሔር፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት ብዝሃነት መልኮቿ ገጾቿ፣ ውበቷ፣ በረከቶቿ በአግባቡ ማስተናገድ ለሕብር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ትናንት ነጻነታችንን በደማችንና በአጥንታችን ማስከበር የቻልነው ሕብራዊ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተደምሮ በአንድነት በመቆሙ መሆኑን ገልጸው፤ የተለያዩ የውስጥና የውጭ ጫናዎች ተቋቁመን የሀገራችንን ህልውና ማስጠበቅ የቻልነው በሕብር ነው ብለዋል።
የላባችን ውጤት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መገባደድ ደረጃ ላይ መድረስ የቻለው ሀገራዊ አቅማችን ደምረን በሕብር ስለሰራን ነው ሲሉ ገልጸዋል።
አደጋዎች ሲገጥሙ መሻገር የሚቻለው በሕብር መሆኑን ጠቅሰው፤ በጎፋ ዞን የተከተሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ኢትዮጰያውያን በሕብር እንዴት እንደቆምን ማሳያ ነው ብለዋል።
ቀጣይ ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት ጠንካራና ሉዓላዊነቷና ብልጽግናዋ የተረጋገጠ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባት የሚሚቻለውም በህብር መሆኑን መግለጻቸውን ከፓርቲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ፓርቲው በህብር የተፈጠረ፣ በሕብር የሚያምን እንደዚሁም ሕብርን ለማጽናት የሚታገልና ራሱ በህብር የሚጸና ፓርቲ ነው ብለዋል፡፡