Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የወል ትርክትን በማጽናት ለሀገራችን ብልጽግና እንረባረብ – አቶ ጥላሁን ከበደ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ወቅታዊ ፈተና የሆነው ነጠላ ትርክት ቦታና ጊዜ እንዳያገኝ በማድረግ በወል ትርክት ወንድማማችነትን በማጽናት በጋራ ለሀገራችን ብልጽግና ልንረባረብ ይገባል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሠ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡

የኅብር ቀን “ኀብራችን ለሰላማችን” በሚል መሪ ሐሳብ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተለያዩ መርሐ-ግብሮች እየተከበረ ነው፡፡

ርዕሰ መሥተዳድሩ ዕለቱን አስመልክተው በአስተላለፉት መልዕክት÷ በወንድማማችነት የወል ትርክታችንን አጽንተን በዘመናት ያካበትናቸውን የአንድነት፣ የመቻቻል እና የመተሳሰብ እሴቶችን አጎልብተን በጋራ ጥረት ጊዜያዊ ፈተናዎችን በብቃት እንሻገራለን ብለዋል።

ብዘኀነት ለጥንካሬያችን ምንጭ፣ የውበታችን ምስጢር እና ለስኬታችን መሰረት ነው ሲሉ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡

የጋራ አጀንዳችን የሀገራችንን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ውጥኖች ስኬት በትብብርና በመተማመን መረባረብን ይጠይቃልም ነው ያሉት፡፡

ስለዚህ ወቅታዊ ፈተና የሆነው ነጠላ ትርክት ቦታና ጊዜ እንዳያገኝ በማድረግ በወል ትርክት ወንድማማችነትን በማጽናት በጋራ ለሀገራችን ብልጽግና እንረባረብ ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡

ዕለቱ በተለያዩ ሁነቶች የሚከበር ሲሆን÷ የክልሉ፣ የዞኑና የወላይታ ሶዶ ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት በማስ ስፖርት መከበር ጀምሯል።

በተመሳሳይ በክልሉ ክላስተር መቀመጫ በሆኑ ከተሞች ማስ ስፖርትን ጨምሮ በተለያዩ ሁነቶች ዕለቱ ሲከበር እንደሚውል ተመላክቷል።

Exit mobile version