አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ከሚል፣ የቀድሞው የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ እንዲሁም የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በፈረንጆቹ ከታህሳስ 14 አስከ 15 በኳታር በሚካሄደው 19ኛው የዶሃ ፎረም ላይ ለመሳተፍ ዶሃ ገብተዋል።
ከፎረሙ አስቀድሞም የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ከሚል እና የቀድሞው የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በዛሬው እለት በዶሃ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ዓለም አቀፍ ት/ቤትን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱም በኳታር የኢትዮጵያ አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ እና የሚሲዮኑ የስራ ባልደረቦች፣ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ማህበር አመራሮች፣ የተለያዩ አደረጃጀቶች መሪዎች፣ የተማሪ ወላጆችና ቤተሰቦች፣ እንዲሁም ሕጻናት ተገኝተዋል።
የኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤቱ እድሳት በፍጥነት እና በጥራት እየተከናወነ ሲሆን፣ የእድሳት ሥራው በሚቀጥሉት ሶስት ሳምንታት ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ሥራውን የሚያከናውነው ተቋራጭ ኃላፊዎች በጉብኝቱ ወቅት ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቱም በቀጣዩ የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራውን ይጀምራል ነው የተባለው።
የኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤቱ እንዲቋቋም በ 2010 ዓ.ም ለኳታር መንግስት ጥያቄውን በማቅረብ አወንታዊ ምላሽ እንዲሰጥ ያደረጉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ መሆናቸውን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት አስታውቋል።