አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ ክ/ከተሞች የተገነቡ 837 መኖሪያ ቤቶችን ለአቅመ ደካሞችና ለሀገር ባለውለታ ነዋሪዎቻች አስተላልፏል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዳሉት÷በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብተው ለነዋሪዎች ከተላለፉ ቤቶች ውስጥ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በየካ ክፍለ ከተማ የገነባቸው 54 ቤቶች ይገኛሉ፡፡
በተጨማሪም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ በተለያዩ ባለሃብቶች 108 ቤቶችና በአራዳ ክ/ከተማ በአብዱለጢፍ ዑመር ፋውንዴሽን (አሚባራ ግሩፕ) 32 ቤቶች መገንባታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ከንቲባዋ ነዋሪዎች አዲስ ዓመትን በአዲስ ተስፋ እንዲጀምሩ ትልቅ አስተዋፅዖ ላበረከቱ ተቋማትና የከተማዋ ልበ ቀና ባለሃብቶች ምስጋና አቅርበዋል፡፡