የሀገር ውስጥ ዜና

ርዕሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ የሉዓላዊነት ቀንን ስናከብር ዋጋ ከፍለው ሀገር ያቆዩትን በመዘከር ነው አሉ

By Meseret Awoke

September 08, 2024

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሉዓላዊነት ቀንን ስናከብር ዋጋ ከፍለው ኢትዮጵያን ያስቀጠሉ ባለታሪኮችን በመዘከር ነው ሲሉ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መሥተዳደር ሙስጠፌ መሐመድ ገለጹ፡፡

የሉዓላዊነት ቀን ጳጉሜን 3 “ኀብር ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ሐሳብ በክልሉ እየተከበረ ነው፡፡

በአከባበሩ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ሙስጠፌ÷ ለሀገራቸው ዋጋ ለከፈሉ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዱ ክስተቶች ሲፈጠሩ ኢትዮጵያውያን አንድ በመሆን ሀገራቸውን የመጠበቅ ታሪክን ሊያስቀጥሉ እንደሚገባም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ሉዓላዊነት ሙሉ የሚሆነው የሀገር ዳር ድንበርን ከመጠበቅ በተጨማሪ ከኢኮኖሚ ተረጂነት ነፃ መውጣት ሲቻል ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡

በዚህም በስንዴና ሩዝ ሰብል ላይ የተጀመሩ ዘርፈ-ብዙ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ነው ያሉት፡፡