Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ የዜጎች ተሳትፎ ወሳኝ ነው – አምባሳደር ታዬ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የዜጎች ተሳትፎ ወሳኝ ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ገለጹ፡፡

ጳጉሜን 3- የሉዓላዊነት ቀን ለሀገር ሉዓላዊነት መከበር ለተከፈለ ዋጋ ክብር በመስጠት በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚዬም እየተከበረ ነው፡፡

በአከባበርሥነ-ሥርዓቱ ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ፣የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሃመድ (ኢ/ር)፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ፣ ሚኒስትሮች፣ የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

አምባሳደር ታዬ በመድረኩ እንዳሉት÷ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ሉዓላዊነቷን አስከብራ የኖረች ሀገር ናት ፤ ለዚሁ ሉዓላዊነቷ ዋነኛው ማሳያ በዓድዋ ድል የነበረው ጀግንነት ነው ብለዋል።

በሁሉም ዘርፎች ሉዓላዊነቷ የተረጋገጠች ሀገር መፍጠር እንደሚያስፈልግ ገልጸው ፥ይህም የሁሉንም ዜጎች ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ገልፀዋል።

በተለይ ሀገሪቱ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ከድህነት አዙሪት እና ከተረጅነት ቀንበር እንድትወጣ መትጋት የትውልዱ ተግባር ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በቴክኖሎጂ እድገት ሀገሪቱን ከፍ በማድረግና አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን ማረጋገጥ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በዲፕሎማሲው፣ በፖለቲካውና በሌሎችም ዘርፎች ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ የእያንዳንዱን ተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር መተግበር ያስፈልጋል ነው ያሉት አምባሳደሩ።

የሀገርን ዳር ድንበር ማስከበርና ሰላሟን ማስጠበቅ አንዱ የሉዓላዊነት ተግባር በመሆኑ ጠቁመው÷ ይህን አጠናክር ማስቀጠል እንደሚያስፈልግም እጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በሳሙኤል ወርቃየሁ

Exit mobile version