Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በአዳማ ከተማ የሉዓላዊነት ቀን በወታደራዊ የሰልፍ ትርዒት እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዳማ ከተማ የሉዓላዊነት ቀን በተለያዩ ወታደራዊ የሰልፍ ትርዒት እየተከበረ ይገኛል፡፡

የሉዓላዊነት ቀን “ህብር ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ሀሳብ ነው እየተከበረ የሚገኘው።

ቀኑ እየተከበረ ያለው በለውጥ ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የተገዳደሩ ፈተናዎችን በመቋቋም የሀገርን አንድነትና ሉዓላዊነት ለማፅናት የተሰሩ ሥራዎችን በማሳብ እንደሆነ ተገልጿል።

በዓሉ በተለያዩ ወታደራዊ የሰልፍ ትርዒት እየተከበረ ሲሆን ፥ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራል ፖሊስና የክልሉ ፖሊስ አባላት ተሳትፈዋል።

በአከባበር ሥነ-ሥርዓቱ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ-ጉባኤ ሰዓዳ አብዱራሃማን፣ ምክትል አፈ ጉባኤ ኢሊያስ ዑመታ፣ የክልሉ የፀጥታ ክላስተር አመራር አባላት ተገኝተዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ዛሬ በመንግሥትና በግል ተቋማት ሰንደቅ ዓላማ በመስቀል ሁሉም ሰው ባለበት ቆሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር የሚዘምርበት ሥነ-ሥርዓት እንደሚኖር የዘገበው ኢዜአ ነው።

Exit mobile version