የሀገር ውስጥ ዜና

እኛ ኢትዮጵያዊያን በሌሎች ጉዳይ ጣልቃ የማንገባ፤ በሉዓላዊነታችንም የማንደራደር ሕዝቦች ነን – አቶ አረጋ ከበደ

By Melaku Gedif

September 08, 2024

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እኛ ኢትዮጵያዊያን በሌሎች ጉዳይ ጣልቃ የማንገባ፣ በሉዓላዊነታችንም የማንደራደር የትብብር ሚዛንን መራጭ ሕዝቦች ነን ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ፡፡

አቶ አረጋ ጷጉሜ 3 የሉዓላዊነት ቀንን አስመልክተው ባለስተላለፉት መልዕክት÷ ኢትዮጵያዊያን የቀደምት ስልጣኔዎች ባለቤቶች ስንሆን ከተቸገረ ጋር መተጋገዝን እንዲሁም በእብሪትና ፀብ አጫሪነት ለሚነሱ አካላት ደጋግመው እንዲያስቡ የሚያደርጉ ምላሾችን በመስጠትም የምንታወቅበት መለያችን ነው ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ቀኑን አስመልክተው ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

እኛ ኢትዮጵያዊያን በሌሎች ጉዳይ ጣልቃ የማንገባ፣ በሉዓላዊነታችንም የማንደራደር የትብብር ሚዛንን መራጮች ነን!

የእኛ የኢትዮጵያውያን የታሪክ ሰበዞች ሲፈተሹ በማንም የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት፣ ከተቸገሩ ወገኖች ጋር ሁሉ በወንድምነት ትብብር መቆምንና ለሰላም በፅናት ዋጋ መክፈልን የምናውቅ እንዲሁም በራሳችን ነፃነትና ሉዓላዊነት ላይ የሚደረጉ ትንኮሳዎችን በአንድነት የምንቀለብስ የሉዓላዊነት ባለቤቶች ነን።

የቀደምት ስልጣኔዎች ባለቤቶች ስንሆን ከተቸገረ ጋር መተጋገዝን እንዲሁም በእብሪትና ፀብ አጫሪነት ለሚነሱ አካላት ደጋግመው እንዲያስቡ የሚያደርጉ ምላሾችን በመስጠትም የምንታወቅበት መለያችን ነው።

ሉዓላዊነታችንን በፅናት የጠበቅነው፤ በአልደፈር ባይነት ያስከበርነው እንጂ ተጋፊ የሌለበት ሆኖ የዘለቀ አይደለም። የክቡር ታሪክና የተፈጥሮ ፀጋዎች ባለቤት የሆነችው ሀገራችን በተለይም የታላቁ የአባይ ወንዝ ባለቤቶች ከመሆናችን ጋር በተገናኘ በሁሉን ይዤው ምኞት በሚናውዙ፣ በብቸኛ ተጠቃሚነት የስግብግብነት ፍላጎት በተለከፉ ታሪካዊ ጠላቶቻችን እና በዓለም ዙሪያ የሰው ልጅን እኩልነትና ወንድማማችነት በካዱና በራስ ወዳድነት የኢምፔሪያሊዝም እብሪት በተንጠራሩ አካላት የተለያዩ ወቅቶች ላይ በተለያዩ ትውልዶች ወቅት ሉዓላዊነታችንን የመዳፈር ሙከራዎች ተደርገው ያውቃሉ።

እኛ ግን አጥፊዎችን ደጋግመው እንዲያስቡ የሚያደርጉ፣ ተበዳዮችንም ለነፃነታቸው የሚያነቃቁና ሞራላዊና የተግባራዊ ምሳሌነት ያስታጠቁ ድሎችን እየፃፍን በሉዓላዊነት ዘልቃናል።

እኛ ኢትዮጵያውንን የምንጩን ባለቤቶች ከታላቁ አባይ ባለይዞታነት ገለል ማድረግን የተመኙ አካላትን በእብሪት በጫሩት እሳት በጉንደትና ጉራ የጦር አውድማዎች የሰጠናቸው ምላሽ ምንም እንኳን የተዛባ ፍላጎታቸውን ባያስተዋቸውም የቀደመውን የእብሪት እርምጃቸውን ገትተው እንዲኖሩ አድርጓቸዋል።

የዓለምን ሕዝብ የእኩልነት መሰረት ያልተቀበሉና አንዱ በሌላው ላይ የልዩ ብልጫ ባለቤት እንደሆነ አድርገው የተነሱ በተግባርም አህጉራችንን አፍሪካን ጨምሮ የጥቁር የሰው ዘርን ሁሉ በራሱ ቤት ለተራ አገልጋይነት እንኳን ክብር የነፈጉ የቅኝ ቅዛት አራማጆችን ክንድ በተባበረ ምላሽ ሰብረን የእኩልነትንና የጥቁር ሕዝቦችን የታሪክ ሰሪነት ማህተም ዳግም የመታንበት የታላቁ የአድዋ ድል በዓል ደግሞ ከእኛ አልፎ በመላው የጥቁር ዘሮች ሁሉ የሉዓላዊነት ምልክት ሆኖ ይኖራል።

የጣሊያን የዳግም ወረራ እርምጃንም በአልበገበር ባይነት የተወጡ አባቶች ያሉን የነፃነት ባለቤቶች ነን። ብዙዎችንም ለነፃነትና ሉዓላዊነት አብቅቷል። እነዚህን ጉልሃን ጠቀስን እንጂ የማንንም ሉዓላዊነት ያለመንካትና በሉዓላዊነታችን ሲመጡብንም በእምቢ ባይ አርበኝነት የድል አድራጊነት ታሪካችን የትውልዳችን የኋለኛ አባቶች ወረቶችና ዛሬም በደማችን የታተሙ ሀቆች ናቸው።

በሌላ መልኩም ከዓለም ዙሪያ ሁሉ ለሰላም ጉዳይ ትብብራችንን ለጠየቁ ሁሉ አዎንታዊ ምላሽ ሰጭዎች ነን። ከቀደመው የኮሪያ የሰላም ማስከበር የአባቶቻችን ስምሪት እስካሁኑ ዘመን የሱዳንና የሶማሊያ የሰላም ማስከበር ግዳጆች በብቃት የምንወጣ ብቻም ሳንሆን በፍትሃዊነታችን እና እውነተኛ የሰላም ዘብነታችን ወዳጅ ቀርቶ ጠላት ይመሰክርልናል። በዚህም መነሻ በተለይም በቀጠናችን ምስራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ ያለን ቦታ ደግሞ እጅጉን ከፍ ያለ ሆኖ እናገኘዋለን።

የኛ የኢትዮጵያዊያን ሌላው ጉልህ መለያችን ችግር ላይ የወደቁ አካላትን ደግፎ ማቋቋም እንጂ ገፍቶ የመጣል ፍላጎትም ድርጊትም የማይጎበኘን በእኩልነትና ወንድማማችነት እንዲሁም በትብብር የምናምን መሆናችን ነው። በቀጠናችን በሀገራት ውስጥም ይሁን በሀገራት መካከል ችግሮች ሲያጋጥሙ ለአስማሚነት ቅድሚያ የሚያስጠራንም ይኸው የጎለበተ አዎንታዊ ሚናችን ነው። እኛ ቅድሚያ ለጎረቤት የምንል እድገትና ሰላማችንንም በትብብር ማሳካት የምንፈልግ ፍትሃዊ ሕዝቦች ነን።

በዓለም ላይ ያፈጠጠውን የቅኝ ግዛት ፕሮጀክት ያመከንን እንዲሁም በሉዓላዊነታችን የማንደራደርና የአፍሪካም ወሳኝ አሰባሳቢ ሀይል መሆናችን በጠላቶቻችን ዘንድ የፈጠረውን ስጋትና ቁጭት ተከትሎ ግን በየዘመኑ የስውር ሴራ ሽረባዎች አላባሩም። በዚህም እኛን ፊት ለፊት ማሸነፍ እንደማይሳካላቸው የገመገሙ ታሪካዊ ጠላቶቻችን እንቅልፍ አጥተው የሚሰሩበት አሁናዊ ባህሪ መነሻቸው እርስ በርስ አጋጭቶ ማዳከም ነው።

እኛ የዚህ ዘመን ትውልዶች ልናስተውለው የሚገባን ጉዳይ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅሞችና የሉዓላዊነት ሞገስ በየትኛውም አነስተኛ ጉዳዮች ለድርድር ማቅረብ የማይገባን መሆኑን ነው። የሀሳብም የፍላጎትም ይሁን የአተያይ ልዩነቶች ሁሌም ነበሩ፣ አሉ ቀጣይም ይኖራሉም።

ጠላቶቻችን ደግሞ እነዚህን ልዩነቶች ማስፋትና ማጉላት ላይ ሳይታክቱ የሚሰሩ፣ የመጋጨታችንን ሂደት የሚጠባበቁና የአንዱ ወዳጅ የሌላውም ጠላት መስለው ገብተው የሚያባብሱ ናቸው። ጠላቶቻችን በሁላችን ፊት ለፊት የማይመጡ ይልቁንም ጥቂት ባንዳዎችን መልምለው በስውር አሰማርተውና በጀት ሳይቀር ደግፈው ሌሎችን በስሜት ማዕበል በመቆስቆስ ለደም መፋሰስ አበክረው የሚሰሩ ናቸው።

የኢትዮጵያ ጠላቶች የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጠላቶች እንጂ የማንም ወዳጅ የማይሆኑ የአዳክሞ መጣል ፍላጎታቸው ቋሚ ተሰላፊዎች ናቸው። ሳይረዱት የቆዩትና ዛሬም ያልገባቸው ነገር ግን የቱም አይነት ልዩነት በታላቋ ሀገራችን ሉዓላዊነት ጉዳይ እንደማያለያየን ነው።

እንደ ብዙ ትናንቶቻችን ሁሉ ዛሬም በማንም ጉዳይ ጣልቃ አንገባም፤ ለማንምና በምንም ሁኔታ በሉዓላዊነታችንም ላይ አንደራደርም!

የተወደዳችሁ የክልላችን እና የሀገራችን ሕዝቦች እንኳን ለሉዓላዊነት ቀን አደረሳችሁ አደረሰን!