አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰው ተኮር አገልግሎት ለመስጠት እና ጤናማና አምራች ዜጋ ለማፍራት ባለድርሻዎች ተቀናጅተው ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ደስታ ሌዳሞ አስገነዘቡ።
በክልሉ ጤና ቢሮ ትኩረት የሚሹ እና ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በሐዋሳ ከተማ የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ እንደተናገሩት÷ በክልሉ ልዩ ትኩረት ከሚሹ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መካከል የጤናው ዘርፍ ዋነኛው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይም በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን የማረም ሥራው የአንድ ተቋም ብቻ አለመሆኑ አስረድተዋል፡፡
ሰው ተኮር አገልግሎት ለመስጠት እና ጤናማና አምራች ዜጋ ለማፍራት በየደረጃው ያለው አመራር እና ባለድርሻዎች ተቀናጅተው በመስራት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ እስገንዝበዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሰላማዊት መንገሻ÷ የመድረኩ አላማ የህብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ የተቀረፁ እና የተተገበሩ ኢኒሼቲቮች ያመጡት ለውጥ ምን እንደሆነ በመለየት በቀጣይ በሚሰሩ ስራዎች ላይ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ነው ብለዋል።
የመድሐኒትና የግብዓት አቅርቦት፣ የወባ በሽታ መስፋፋት፣ የኮሌራ በሽታ እና ሰው ተኮር አገልግሎት የሚሉት ርዕሰ-ጉዳዮች በምክክር መድረኩ ላይ ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውንም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡