አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ዛሬ በአዋሬ መንደር የተገነቡ 275 ቤቶችን ቁልፍ ለነዋሪዎቹ አስረክበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው÷ ዛሬ የአዋሬ አካባቢን ለማሻሻል ላለን ትልም እና ጥረት አንድ ምዕራፍ ሆኗል ብለዋል፡፡
የተጎዳ እና የተጎሳቆለ የነበረው አካባቢ ዛሬ ለነዋሪዎች በተለይም ለአረጋውያን ምቹ እና ለሰው ልጅ የከበረ አኗኗር የሚመረጥ ሰፈር ሆኗልም ነው ያሉት፡፡
ይህ ሥራ የማኅበረሰባችንን አኗኗር ለመለወጥ ላለን ጽኑ አላማ ማሳያ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ አዋሬ ጥራትን ሳያጓድሉ በፍጥነት የመገንባት መርሃችንን ያንፀባርቃል ብለዋል፡፡
አሁን በአዋሬ ክብር ላለው የሰው ልጅ ኑሮ የተመቸ የልጆች መጫወቻ ስፍራ፣ ለማረፊያ እና ማሰቢያ የሚሆን አረንጓዴ ስፍራ፣ ለአረጋውያን የሚመች የእግረኛ መንገድ እንዲሁም ንፁህ ከባቢን ይዟል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ይሁንና በአዋሬ ያሳካነው ገና ጅምር ሥራ ነው፣ በዚህ ሥራችን ረክተን መቆም የለብንም፣ ብዙ ሥራ ይቀረናል፣የብዙ ሚሊየኖች ሀገር እንደመሆናችን በመላው ሀገራችን የዜጎቻችንን ሕይወት ከፍ ማድረግ ፋታ የማይሰጥ ቀጣይነት ያለው ሥራችን ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
መሻሻልን ሳናቋርጥ ለመቀጠል እና ጅምር ሥራውን ለማስፋፋት ከግሉ ዘርፍ እና ከየከተሞች ጋር ያለንን ትብብር ማጠናከር ይኖርብናል በማለት ገልጸዋል፡፡
አዲሱን ዓመት ስንቀበል ብዙዎቹን ተግዳሮቶቻችንን ተሻግረን ለልጆቻችን ጠንካራ ኢትዮጵያን እንደምንገነባ እምነቴ ጽኑ ነውም ብለዋል።