የሀገር ውስጥ ዜና

ተግባራዊ የተደረጉ የሪፎርም ስራዎች ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚ መገንባት ያስቻሉ ናቸው- አቶ አደም ፋራህ

By Feven Bishaw

September 07, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት የለውጥ ዓመታት ተግባራዊ የተደረጉ የሪፎርም ስራዎች ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚ መገንባት ያስቻሉ ናቸው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ተናገሩ።

ጳግሜን 2 የሪፎርም ቀን “ሪፎርም ለላቀ አገልግሎት” በሚል መሪ ሃሳብ በሳይንስ ሙዚየም የፓናል ወይይት እየተካሄደ ነው።

አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት÷ በየዘርፉ ተግባራዊ የተደረጉ የለውጥ ስራዎች ችግሮችን ተቋቁሞ ዘላቂ ዕድገትን ማረጋገጥ ያስቻለ ውጤት የተገኘበት ነው።

በኢኮኖሚው መስክ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የኑሮ ውድነትን ችግር መቀነስ፣ የወጭ ንግድ ሚዛንን ማስተካከል ላይ የተወሰዱ እርምጃዎች ውጤት ያመጡ ናቸው።

ተግባራዊ የተደረጉ የገንዘብ ፖሊሲዎች፣ የብድርና የዕዳ ጫናን ለመቀነስ የተከናወኑ ተግባራት ስኬታማ ሆነዋል፤ የታክስ ፖሊሲውም የመንግስት ገቢ እንዲጨምር አድርጓል ብለዋል።

ከትምህርት ጋር በተያያዘ ከ30 ሺህ በላይ የአጸደ ህጻናት ትምህርት ቤቶችን ከመገንባት ባሻገር በሚሊየን የሚቆጠሩ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ከትምህርት ጥራት ጋር በተገናኘም አዳዲስ አሰራሮችን መዘርጋት፣ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ስራዎችም እንዲሁ ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል።

እንደ አቶ አደም ገለጻ በፍትህ ዘርፉ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መርህን የተከተሉ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ስራዎች ተከናውነዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡