አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምስራቅ እዝ ወራሪና ተስፋፊዎችን አንገት ያስደፋ ጀግና እዝ ነው ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ፡፡
የምሰራቅ ዕዝ 47ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በሐረር ከተማ “የምስራቁ ጮራ የኢትዮጵያ ወታደሮች ነን” በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ነው።
በሐረር ኢማም አሕመድ ስታዲየም እየተካሄዳ ባለው የአከባበር ሥነ-ስርዓት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ፣ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ፣የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃርና ሌሎች አመራሮችም በበዓሉ ላይ ታድመዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በዚህ ወቅት ÷በቀ ጣናው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ለአንዳንድ አምባገነኖች የጦር ድጋፍ በማድረግ ከሦስት ጊዜ በላይ ኢትዮጵያን መውርራቸውን አስታውሰዋል።
ሆኖም ግን ጀግናው ምስራቅ እዝ ከሌሎች የኢትዮጵያ ጀግና ሠራዊት አባላት ጋር በመሆን ወራሪዎችና ተስፋፊዎችን ድባቅ መቷቸዋል ነው ያሉት።
ምስራቅ እዝ ወራሪና ተስፋፊዎችን አንገት ያስደፋ ጀግና እዝ ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ÷ዛሬም እዙ ጀግንነቱን አጠናክሮ የሚያስቀጥልበትና አዳዲስ ጀግኖች የሚፈጥርበት ወታደራዊ አቅምና ቁመና ፈጥሯል ብለዋል።
ወራሪዎች ከሀገር ውስጥ ባንዳዎች ጋር በማበር ወረራ ለመፈጸም ቢሞክሩም ኢትዮጵያ ጦርነትን በአጭር ጊዜ ለመመከትና ድል ማድረግ የሚችል ሠራዊት ያላት መሆኑን ዳግም ለማረጋገጥ እወዳለሁ ሲሉ አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
በእዮናዳብ አንዱዓለም