Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ለጎፋ ዞን ተጎጂዎች ቋሚ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ሥራ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በጎፋ ዞን በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች ቋሚ የመኖሪያ ቤት ግንባታ አስጀምረዋል፡፡

አቶ ጥላሁን በዚህ ወቅት እንደገለጹት÷የክልሉ መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለተጎጂዎች በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

ዋና ትኩረትን ችግሩን በዘላቂነት መፍታት ላይ በማድረግ በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱንም ነው የተናገሩት፡፡

በዛሬው የመሻገር ቀንም የተፈናቃሉ ወገኖች ከአደጋ ስጋት ቀጠና ውጪ በሆነ አካባቢ እንዲኖሩ ቋሚ የመኖሪያ ቤት ግንባታ በይፋ መጀመሩን አብስረዋል፡፡

ኅብረት አንድነታችን አጠንክረን ተባብረን ከሰራን የትኛውንም ችግር መሻገር እንችላለን ሲሉ መግለጻቸውንም የርዕሰ መስተዳድሩ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

አደጋውን ተከትሎ መላ ኢትዮጵያዊያን፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ሌሎች አጋር አካላት ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

Exit mobile version