አዲስ ዓመት ያለቀውን ዓመት ሸኝቶ አዲሱን ከመጀመርም ባለፈ ከአስቸጋሪው ደመናማ የዝናብ ወቅት ወደ ብሩህ ተስማሚ ወራት መሻገርን የሚያበስር፣ በአዲስ አስተሳሰብና በብሩህ ተስፋ የምንቀበለው የአዲስ ምዕራፍ መባቻ ነው።
የተገባደደው ዓመት እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ከተማ በበርካታ መስኮች የህዝባችንን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት የማረጋገጥ ጉልህ ፋይዳ ያላቸው ዘርፈ ብዙ ውጤቶች ያስመዘገብንበት እንዲሁም ከድህነት ወደ አስተማማኝ የብልጽግና ምዕራፍ ለመሸጋገር የሚያስችለንን መሰረት የጣልንበት አንጸባራቂ የስኬትና የእድገት ዘመን እንደነበረ ግልጽ ነው።
ይህ ዛሬ የምናከበረው የመሻገር ቀንም፣ ባለፈው ዓመት ካለፍናቸው ትላልቅ ፈተናዎችና በድል ከተሻገርናቸው እንቅፋቶች ተገቢውን ትምህርት ወስደን በዚህ ሂደት ውስጥ አቅም በፈቀደ መጠን አስተዋጾ ያደረጉና ያገዙን አካላትንና መላው ህዝባችንን ከልብ የምናመሰግንበት፣ ብሎም የቀጣዩ ዓመት የርብርባችን ማዕከል የሆነውን ብልጽግናን የማረጋጋጥና ህዝባችንን ወደ ላቀ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እመርታ የማሻገር ራዕይ እውን ለማድረግ በጋራ ለመትጋት ቃል የምንገባበት ዕለት ነው።
በመሆኑም፣ ባሳለፍናቸው የለውጥ ዓመታት በአጭር ጌዜ ያስመዘገብናቸውን ተአምራዊ የልማት ስኬቶች ተስፋ ሰጪነት አይቶ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሁሉ በመሳተፍ ሲያግዘንና ሲያበረታን የነበረው ህዝባችን ላሳየን አጋርነትና ትብብር ሁሉ ልባዊ ምስጋና እያቀረብን ቀጣዩ ዓመትም ካሳለፍነው ዓመት የተሻሉ ግዙፍ ድሎችን በማስመዝገብ ህዝባችንን ወደ ብልጽግና የምናሻግርበት እንደሚሆን በመተማመን ይህን ታላቅ ሀገራዊ ራዕይ ለማሳካት ህዝባችን አብሮን እንዲቆም ጥሪ እናስተላልፋለን።
መልካም አዲስ አመት!!!!”
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ