አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመሻገር ቀንን ስናከብር ያገኘናቸውን ሁለንተናዊ ስኬቶች በማስቀጠል ሊሆን ይገባል ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።
የመሻገር ጥሪቶች፤ የአዲስ ብርሃን ወረቶች” በሚል መሪ ሃሳብ ጳጉሜን -1 የመሻገር ቀን እየተከበረ ነው፡፡
በአቶ አሻድሊ ሀሰን የተመራ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ልዑክም በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ጊጺ ቀበሌ በክላስተር የለማ ሰብልን በመጎብኘት ቀኑን እያከበረ ይገኛል፡፡
አቶ አሻድሊ በዚህ ወቅት÷ የመሻገር ቀንን ስናከብር ያገኘናቸውን ሁለንተናዊ ስኬቶች በማስቀጠል ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የተፈጠረውን ሠላም በመጠቀም በዳንጉር ወረዳ የሰሊጥ፣ በቆሎ፣ አኩሪ አተር፣ ማሽላና ሌሎች ሰብሎች በሰፋፊ ማሣዎች ላይ እየለሙ እንደሚገኙ መግለጻቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በዳንጉር ወረዳ በምርት ዘመኑ ለማልማት ከታቀደው 92 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን 90 ነጥብ 9 ሺህ ሄክታሩ በዘር መሸፈኑ ተገልጿል።