አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) “የመሻገር ጥሪቶች፤ የአዲስ ብርሃን ወረቶች” በሚል መሪ ሃሳብ ጳጉሜን 1 የመሻገር ቀን እየተከበረ ነው፡፡
ቀኑ ሲከበርም ኢትዮጵያን ለማሻገር በተደረጉ ጥረቶች፣ የተገኙ ስኬቶች እየታሰቡ ነው፡፡
በሁሉም ዘርፎች ኢትዮጵያን ለማሻገር ትልቅ አቅም የፈጠሩ ስኬቶች ቢመዘገቡም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የተመዘገቡ ድሎች ለመሻገር ቀን የመሻገር ምልክት ናቸው፡፡
በዚህም ወደታችኛው የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ተጨማሪ ብስራት ከጉባ ተደምጧል።
3ኛ እና 4ኛ ተርባይኖች ሥራ መጀመራቸውን እንዲሁም የወንዝ ፍሰት ሳይስተጓጎል ከመቀጠሉም በተጨማሪ የግድቡ የውሃ ማስተንፈሻ በሮች ተከፍተው ተጨማሪ 2 ሺህ 800 ሜኪ ውሃ በሰከንድ ማፍሰስ መጀመራቸው ተበስሯል።
የኢትዮጵያውያን የጋራ አሻራ ውጤት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ የመሻገር ምልክቶች ውስጥ በዋነኛነት ይጠቀሳል።