አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ተሞክሮዎችን በመውሰድ ለቀጣይ ድሎች መታጠቅና ብርቱ ተስፋን መሰነቅ ያስፈልጋል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ ጳጉሜን 1 “የመሻገር ቀንን” አስመልክቶ የተዘጋጀውን የምክክርና እውቅና መርሐ ግብር አስጀምረዋል።
በመርሐ ግብሩ ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ እና በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህን ጨምሮ ሚኒስትሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በመድረኩ “የመሻገር ጥሪቶች፤ የአዲስ ብርሃን ወረቶች” በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ዘርፎች በተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች የተገኙ ውጤቶች፣ ተግዳሮቶችና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን የሚዳስስ ዘጋቢ ፊልም ቀርቧል።
የውሃና ኢነርጅ ሚኒስቴር ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከቱት ለመከላከያ ሰራዊት፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ የፋይናንስ ተቋማትን በመወከል ብሄራዊ ባንክ፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ለስፖርትና የኪነ ጥበብ ዘርፉ፣ ለሃይማኖት ተቋማት፣ በግንባታው የተሳተፉ ሰራተኞችና ባለሙያዎች፣ ለመገናኛ ብዙሃንና ለንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት እውቅና ሰጥቷል፡፡
በተመሳሳይ የግብርና ሚኒስቴር ለክልሎች፣ ለሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተቋማት እውቅና የሰጠ ሲሆን÷ በንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ደግሞ ኢትዮጵያ እንድትሻገር አስተዋጽኦ ላበረከቱ የግል ተቋማትና ድርጅቶች እውቅና ተሰጥቷል።
ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ÷ በተገኙ ድሎች ሳንኩራራና በሚገጥሙን ፈታናዎች ሳንደናቀፍ በጀመርነው የእድገትና ብልጽግና ሃዲድ በፍጥነት በመጓዝ አሻግረን ወደተመለከትነውና በጥልቀት ወደ ተመኘነው መዳረሻችን መገስገስ ይገባናል ብለዋል፡፡
በዚህም ቀደም ሲል የምንታወቅበትን ድህነትና ኋላ ቀርነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወደግ አለብን ሲሉ አጽንኦት ስጠተዋል፡፡
በፍሬሕይወት ሰፊው