የሀገር ውስጥ ዜና

ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ዕድሳት የተደረገለትን የሀረር ቤተ መንግስት መርቀው ከፈቱ

By amele Demisew

September 06, 2024

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ዕድሳት የተደረገለትን የሀረር ቤተ መንግስትና አዲስ የተገነባውን የምስራቅ ጮራ ሁለገብ አዳራሽ መርቀው ከፈቱ።

የምስራቅ ዕዝ 47ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡

በአገልግሎት ምክንያት አርጅቶ የነበረው የሀረር ቤተመንግስት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ታድሶ በጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ተመርቆ ተከፍቷል፡፡

በተጨማሪም በዕዙ መሀንዲስ መምሪያ የተገነባውና በ7 ሺህ 400 ካሬ ላይ ያረፈ አዳራሽ ተጠናቆ ለምረቃ መብቃቱ ተመላክቷል፡፡

አንጋፋውን የምስራቅ ዕዝ የሚዳስሱ የፎቶ አውደ ርዕይም በእንግዶች መጎብኘቱን ከመከለከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በምረቃ ዝግጅቱ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን እና ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰን ጨምሮ ሌሎች የክልሉና የሰራዊቱ አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡