አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 750 ሺህ ቤተሰቦችን በሶላር ሆም ሲስተም ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክና የብርሃን ተደራሽነት ፕሮግራም በዓለም ባንክ በሚደገፍ የ50 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር በጀት በአምስት ዓመታት ከዋናው ኤሌክትሪክ መስመር ርቀው የሚገኙ 750 ሺህ አባዎራዎችን ነው ተጠቃሚ ለማድረግ ማቀዱ የተገለጸው፡፡
ፕሮግራሙ በአምስት ዓመታት ውስጥ ገጠራማ የሆኑና ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ከ2 ነጥብ 5 አስከ 50 ኪሎሜትር ርቀው የሚገኙ አባዎራዎችን የሶላር ሆም ሲስተም ተጠቃሚ ለማድረግ ታላሚ ተደርጎ የሚተገበር ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይ ሁለት ዓመታት በፕሮግራሙ በኢትዮጵያ 400 ወረዳዎች 350 ሺህ አባዎራዎችን የሶላር ሆም ሲስተም ተጠቃሚ ለማድረግ 10 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ተበጅቶ ወደ ተግባር ተገብቷልም ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፡፡
የመጀመሪያ ዙር የፕሮግራሙ አካል የሆነውን በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ከ45 ሺህ በላይ አባዎራዎችን በሠባት ክልሎች የሶላር ሆም ሲስተም ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችለውንና 150 ሚሊየን ብር ወጭ የሚደረግበትን የውል ስምምነት ከዘጠኝ የሶላር ቴክኖሎጂ አቅራቢና አከፋፋይ ሀገር በቀል ድርጅቶች ጋር ተፈርሟል፡፡
በፊርማ ስነስርዓቱ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ( ዶ/ር፣ ኢ/ር) ÷ድርጅቶቹ በገቡት የውል ስምምነት መሰረት ጥራት ያለው ስራ በመስራት ሀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ማሳሰባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተቋማቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም በመግለጽ ፥ ውል የወሰዱ ድርጅቶች ለስራቸው ውጤታማነት ስንቅ የሚሆናቸውን መልካም ስራ በመስራት ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡