የሀገር ውስጥ ዜና

በአዲስ አበባ እየተመዘገበ ያለው ፈጣን እድገት ለአፍሪካ ከተሞች በተምሳሌትነት የሚጠቀስ ነው – የአፍሪካ ሀገራት ተወካዮች

By Shambel Mihret

September 05, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ እየተመዘገበ ያለው ፈጣን እድገት ለሌሎች የአፍሪካ ከተሞች በተምሳሌትነት የሚጠቀስ ነው ሲሉ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ ተወካዮች ገለጹ።

የመጀመሪያው የአፍሪካ የከተሞች ፎረም “ዘላቂ የከተሞች ልማት ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ 2063” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

የተለያዩ የዘርፉ ተወካዩች፣ አጀንዳ 2063 በከተሞች ልማትና አጠቃላይ እድገት በመታገዝ የምንመኛትን አፍሪካ እውን ለማድረግ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በተለይ በመሰረተ ልማት ዘርፍ ሰፊ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ በራስ አቅም፣ ፓርኮችን፣ የኮሪደር ልማትና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መገንባቷን መመልከታቸውን ገልጸዋል።

ደቡብ አፍሪካን በመወከል በፎረሙ እየተሳተፈ ያለው ኮላኒ ማሳኒ÷ኢትዮጵያ በእርግጥም በከተማ ልማት የሚደነቅ ስራ እየሰራች ነው ሲል ተናግሯል።

ከናይጄሪያ የመጡት የፎረሙ ተሳታፊ አማኡ ያና በበኩላቸው÷ከ10 ዓመታት በፊት አዲስ አበባን መጎብኘታቸውን በማስታወስ አሁን ያዩት የከተማዋ እድገት እጅግ እንዳስደነቃቸው ገልጸዋል።

በመንግስታቱ ድርጅት የዩኤን ሃቢታት የፖሊሲ ጥናት ዘርፍ ተወካይ ሬሚ ሲጄፒ÷በአዲስ አበባ ከታዩት የልማት ሥራዎች ለህዝብ የመዝናኛ ስፍራዎች የተሰጠው ትኩረት ቀልብ የሚስብ መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይም የአፍሪካ ከተሞች አረንጓዴና ምቹ እንዲሆኑ ለማስቻል የአዲስ አበባን ተሞክሮ ሊተገብሩ ይገባል ነው ያሉት።