የሀገር ውስጥ ዜና

ሐዋላ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸው ልማት ባለቤት የሚያደርጋቸው ነው – አቶ ማሞ ምህረቱ

By amele Demisew

September 05, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው የሚልኩት ገንዘብ (ሐዋላ) በሀገራቸው ልማት በንቃት እንዲሳተፉና የልማቱ ባለቤት የሚያደርጋቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ‘ደቦ’ በሚል ስያሜ የተዘጋጀውን የውጭ የሐዋላ ፍሰት የሚያስተዋውቅና ግንዛቤ የሚያስጨብጥ አውደ ርእይ የተለያዩ ባንኮች በተገኙበት ተከናውኗል።

በመድረኩ (unite.et) የተባለ መተግበሪያ የተዋወቀ ሲሆን መተግበሪያው የውጭ ምንዛሪ ሒሳብ መክፈትና ገንዘብ ማስተላለፍ የሚያስችል እንደሆነ ተመላክቷል።

በውጭ ምንዛሪ ሒሳብ በተፈለገው መጠን መክፈት የሚቻል ሲሆን ተንቀሳቃሽ፣ የቁጠባ እና በጊዜ የተገደበ የውጭ ምንዛሪ በሚሉ አማራጮች መክፈት እንደሚቻል ነው የተገለጸው።

የውጭ ምንዛሪ ሒሳብ ለመክፈት በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ በኢትዮጵያ የሚኖሩ የውጭ ሀገራት ዜጎች አገልግሎቱን እንደሚያገኙ ተመላክቷል።

ይፋ የሆነው መተግበሪያና የስራ ትግበራ በትክክል ስራ ላይ ለማዋል የባንክ አመራሮችና ሰራተኞች በሃላፊነት እንዲሰሩ አቶ ማሞ አሳስበዋል።

በቅርቡ ተግባራዊ የሆነው የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ በጥብቅ አስተዳደር በመተግበር ላይ እንደሚገኝና በአጭር ጊዜ አበረታች ውጤት መገኘቱን ገልጸው፤ ከተቀመጡ አሰራሮች ውጭ በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ ህጋዊ ያልሆኑ አሰራሮችን በቴክኖሎጂ የታገዘ ቁጥጥርና ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቁመዋል።

በፍሬህይወት ሰፊው