አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሲካሄድ የነበረው የምክክር መድረክ ተጠናቋል።
ምክክሩ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስተባባሪነት ከነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለስድስት ቀናት በሆሳዕና ከተማ ሲካሄድ የነበረ ሲሆን÷ የምክክሩ ባለድርሻ አካላት ያደራጁትን የክልሉን አጀንዳ ለኮሚሽኑ አስረክበዋል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)÷ የክልሉን አጀንዳ ከምክክሩ ባለድርሻ አካላት ተወካዮች ተረክበዋል።
በዚሁ ወቅት ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)÷ ወደምንፈለግበት ደረጃ የምንደረሰው ልዩነትን አቻችለን በመመካከር ነው ማለታቸውን የኮሙሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
ኮሚሽኑም ከክልሉ የምክክር ባለድርሻ አካላት የተረከባቸውን አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ ምክር ቤት በማቅረብ በመመሪያና በአሰራር ስርአቱ መሰረት እንደሚመለከት ገልጸዋል፡፡
በምክክሩ ከክልሉ ወረዳዎች ከ1 ሺህ 400 በላይ ወኪሎችን ጨምሮ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከመንግስት አካላት፣ ከተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንዲሁም ከልዩ ልዩ ተቋማትና ማህበራት የተወከሉ ከ2 ሺህ 400 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡