አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በ114 የስብዕና መገንቢያ ማዕከላት ወጣቶችን በሥነ-ምግባር የማነጽና ያላቸውን ተሰጥኦና ክህሎት እንዲያዳብሩ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የከተማዋ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የመዲናዋ 6ኛው ከተማ አቀፍ የወጣት ስብዕና መገንቢያ ማዕከላት የኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል ውድድር በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ ተካሂዷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ በላይ ደጀን በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የወጣቶችን ስብዕና ለመገንባት በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡
ወጣቶች አዳዲስ ሃሳቦችን የመፍጠርና የመቀበል እምቅ አቅም እና ብሩህ አዕምሮ ስላላቸው ለሀገር እድገት የሚጫዎቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ይህን በመገንዘብም ወጣቶች ከአላስፈላጊ ማህበራዊ ጠንቆች ርቀው በሥነ-ምግባር እንዲታነጹ፣ ያላቸውን ተሰጥኦና ክህሎት እንዲያዳብሩ የሚስችሉ 114 የስብዕና መገንቢያ ማዕከላት በመዲናዋ መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በማዕከላቱም በርካታ ወጣቶች ለቀጣይ ሕይወታቸው ስንቅ የሚሆን ክህሎት እና ተሞክሮ እያካበቱ እንደሚገኙ ነው የገለጹት፡፡
የኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል ውድድሩ ወጣቶች የሀገራቸውን ባህል፣ ወግና ትውፊት ከማስተዋወቅ ባለፈ ሀገር ተረካቢነታቸውን የሚያሳዩበት ነው ብለዋል፡፡