አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅ ዕዝ 47ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በጅግጅጋ ከተማ መከበር ጀምሯል፡፡
በአከባበር ሥነ-ሥርዓቱ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ እና የጦር ሃይሎች ምክትል ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ ተገኝተዋል፡፡
የበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ብርጋዲየር ጀኔራል ኑሩ ሙዘይን÷ ምስራቅ ዕዝ ላለፉት 47 ዓመታት በበርካታ ድሎች ታጅቦ ታሪክ የሠራ ዕዝ መሆኑን አውስተዋል።
ዕዙ ማንኛውንም ግዳጅ መፈፀም የሚችል አስተማማኝ ወታደራዊ ቁመና ላይ እንደሚገኝም ነው ያመላከቱት።
የጅግጅጋ ከተማ ከንቲባ ሻፊ አህመድ (ኢ/ር) በበኩላቸው÷ አሁን ላይ በክልሉ ለተገኘው አስተማማኝ ሰላም ምስራቅ ዕዝ የከፈለው መስዋዕትነት በክልሉ ሕዝብ ዘንድ የማይረሳ ሕያው ታሪክ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የተገኘው ሰላም ቀጣይነት እንዲኖረው የሶማሌ ክልል ሕዝብ ፍቅሩንና ድጋፉን የበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል፡፡