Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሕዝባችንን ከተረጂነት ለማላቀቅ የጀመርነው ጉዞ ፍሬ እያፈራ ነው – አቶ አደም ፋራህ

 

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያን የመሰለ እምቅ አቅም ያላት ሀገር ተችሮን ለእርዳታ እጃችንን ለምጽዋት የምንዘረጋበት ጊዜ ይበቃል ብለን ከተረጂነት እሳቤና ተግባር ለመላቀቅ የጀመርነው ጉዞ ፍሬ እያፈራ ነው ሲሉ አቶ አደም ፋራህ ተናገሩ፡፡

በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው÷ ከተረጂነት እሳቤ ነፃ የሆነ ማህበረሰባዊ ውቅር ገንብተን፣ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን አረጋግጠን፣ የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ለመጎናፀፍ እንድንችል አቅደን ወደ ስራ ገብተናል ብለዋል።

በዚህም ከ10 ነጥብ 6 ሚሊየን ሕዝብ በላይ የተሳተፈበት “ከተረጂነት ወደ ምርታማነት፣ ለሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር” በሚል መሪ ሀሳብ ህዝባዊ መድረኮች በማካሄድ ከህብረተሰቡ ጋር የጋራ መግባባት ተፈጥሮ ኮሚቴዎች ተዋቅረው ወደ ስራ መገባቱን ገልፀዋል።

ሕዝቡ በአርበኝነት ስሜት ልመና በቃኝ ብሎ እንዲነሳና ከተረጂነት በመላቀቅ የተሟላ ነፃነትን እንዲጎናጸፍ የሚያስችል ቁጭት መፈጠሩን አመልክተዋል።

እንደሀገር ሊኖረን የሚገባውን የፖሊሲ ነፃነት እና ተፅእኖ አልባ የሉአላዊነት ህልውና መጎናፀፍ የምንችለው ክብራችንን ለሚሰፈርልን ስንዴ መስዋእት አድርገን ካላቀረብን ብቻ እንደሆነና ከተረጂነት ለመላቀቅም ብቸኛው መፍትሄ ምርታማነትን ማሳደግ እንደሆነ ሕዝባችን ተረድቶታል ብለዋል።

ይህንን መነሻ በማድረግም በግብርናው ዘርፍ በስንዴ፣ በሩዝ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በምግቤን ከጓሮዬ፣ በአረንጓዴ አሻራ እና በሌሎችም የልማት መርሃ ግብሮች የተገኙ ውጤቶችን በማስፋት የልመና እና የተረጂነት እሳቤን ከማህበረሰቡ የሞራል መዝገበ ቃላት ውስጥ ለመፋቅ መንቀሳቀስ ይኖርብናል ሲሉም አፅንኦት ሰጥተዋል።

በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንዲቻል የመንግስት የልማት ፕሮግራሞችን አቀናጅቶ ተግባራዊ በማድረግ፣ በአንዳንድ ክልሎች መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።

ለአብነትም በኦሮሚያ ክልል “ቡሳ ጎኖፋን” የመሰሉ የህብረተሰቡ የመደጋገፍ እና የመረዳዳት፣ በችግር ጊዜ ለወገን የመድረስ ባህልን የሚያሳድጉ እሳቤዎችን፣ ተቋማትንና ተግባራትን በማዳበር፣ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች በአግባቡ ለይቶ ድጋፉን በራስ አቅም ለማቅረብ የሚያስችል ስራ በመስራት እና በቂ የአደጋ ጊዜ መጠባበቂያዎችን በማከማቸት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በምሉእነት መሸጋገር እንደሚገባም ነው የገለፁት።

በደም የተከበረው ሉአላዊነታችንን በላባችን በማፅናት ከተረጂነት በመላቀቅ በራሳችን የምንቆምበትን አውድ መፍጠር ትውልዳዊ ግዴታችን ነውና ለአላማው ግብ መምታት ሁላችንም የሚጠበቅብን ኃላፊነት መወጣት ይኖርብናል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

Exit mobile version