የሀገር ውስጥ ዜና

በጤናው ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል- ዶ/ር መቅደስ ዳባ

By ዮሐንስ ደርበው

September 04, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ መኖሩን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ፡፡

ዶ/ር መቅደስ በቤጂንግ እየተካሄደ በሚገኘው የኢትዮ-ቻይና ከፍተኛ የቢዝነስ ፎረም ላይ በጤው ዘርፍ ያለውን ሁኔታ አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም÷ በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ መኖሩን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በፋርማሲቲዩካል ዘርፍ ብቻ በዓመት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ መኖሩን ጠቁመው÷ በጤናው ዘርፍ 6 ዋና ዋና ዘርፎች ተለይተው አስፈላጊውን መሰረተ ልማት የማሟላት ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

እነዚህም የቴሪሸሪ ጤና አገልግሎት፣ የዲያግኖስትክ አገልግሎት፣ የሕክምና ግብዓቶች ማምረቻ፣ የጤናው ዘርፍ የሰው ሃይል ልማት፣ የቅድመ ድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት እንዲሁም የጤና ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ዶ/ር መቅደስ ዳባ በጤናው ዘርፍ በተለዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለሚሳተፉ  አልሚዎች መንግስት ማበረታቻዎችን ጨምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓትን በመዘርጋት አስተማማኝ የገበያ ሁኔታ እንዲመቻች እየተሰራ እንደሆነ መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡