አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ባፀደቀው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ላይ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር ውይይት ተደረጓል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፤ መድረኩ የአዋጁን እሳቤ በአግባቡ ለመረዳትና ግልፅ ያልሆኑ ጉዳዮችን ለማጥራት እንዲሁም ተጨማሪ ዕሴት ታክስን በፋይናንስ ተቋማት ተግባራዊ ለማድረግ ያሉ ተግዳሮቶችን በመለየት መፍትሔ ለማበጀት ነው ብለዋል፡፡
በአዋጁ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር የተያያዙ ድንጋጌዎች ላይ በገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ የታክስ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት አቶ ዋስይሁን አባተ ለተሳታፊዎች አቅርበዋል፡፡
የፋይናንስ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጁን ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
ከተወያዮች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ፤ መድረኩ ሰብሰብ ያለና ወጥነት ያለው አሰራር እንዲፈጠር ያስችላል ብለዋል።
በመሆኑም በተቋማት መካከል ያሉ የአሰራር አለመጣጣሞችን ለማስተካከል የሚረዳ መሆኑን መግለጻቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ጠቁሟል።