ስፓርት

ለ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ልዑክ ዕውቅናና ሽልማት ተሰጠ

By Meseret Awoke

September 04, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፔሩ -ሊማ በተካሄደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሳትፎ ከፍተኛ ውጤት ለአስመዘገበው የኢትዮጵያ ልዑክ ዕውቅናና የማበረታቻ ሽልማት ተበረከተለት፡፡

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ልዑክ በተሳትፎው 6 የወርቅ፣ 2 የብር እና 2 የነሐስ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ከአፍሪካ 1ኛ ከዓለም 2ኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡

በዕውቅናና ሽልማት መርሐ-ግብሩም የወርቅ፣ ብር እና ነሐስ ሜዳሊያ ለአመጡ አትሌቶች በቅደም ተከተል ለእያንዳንዳቸው 40 ሺህ፣ 25 ሺህ እና 15 ሺህ ብር ተሸልመዋል፡፡

ዲፕሎማ ለአመጡና ለተሳተፉ እንደየ ውጤታቸው የማበረታቻ ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን÷ አሰልጣኞችም እንዳስገኙት ውጤት እስከ 40 ሺህ ብር መሸለማቸውን የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በዚህ ወቅት፥ ቀጣዩ ጊዜ ተስፋ የተሞላበት እንደሆነ ተተኪ አትሌቶች አሳይታችሁናል፤ በውጤቱም የሀገራችንን ክብር አስጠብቃችኋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ፥ የዘንድሮው ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና እስካሁን ከተገኘው ውጤት ከፍተኛ መሆኑን ገልጻለች፡፡

አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ውጤቱ የመናበብ መሆኑን ገልጾ÷ በቀጣይ የዓለም ሻምፒዮናም ቡድኑ ደማቅ ድል ማስመዝገብ እንደሚችል አመላክቷል፡፡

ውጤቱ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የተሠራው ሥራ መልካም ፍሬ ለማፍራቱ ማሳያ ነው ያለችው ደግሞ የልዑኩ መሪ አትሌት መሰለች መልካሙ ናት፡፡