አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ በማድረግ ምሳሌ የሚሆን ሥራ እየሰራች ነው ሲሉ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ ገለፁ።
የመጀመሪያው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡
ወ/ሮ ጫልቲ ሳኒ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር÷ኢትዮጵያ ፎረሙን እንድታዘጋጅ ከተመረጠች ጀምሮ አስፈላጊውን ዝግጅት ስታደርግ መቆየቷን አስታውሰዋል።
ፎረሙ በአፍሪካ ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በትብብርና በቅንጅት ለመፍታት የድርሻችንን የምንወጣበት ነው ብለዋል።
ለአፍሪካ 2063 አጀንዳ እውን መሆን የከተሞችን ዘላቂ ልማት ማረጋገጥ እንዲሁም የክትመት ምጣኔውን ማጣጣም፤ ለዚህም መሥራት ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።
በአፍሪካ እየጨመረ ላለው የሕዝብ ቁጥርና የአየር ንብረት ተጽዕኖ ምላሽ መስጠት የሚችል የከተሞች ዘላቂ ልማት እንደሚያስፈልግ መጠቆማቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ከተሞች ፅዱና ለነዋሪዎች ምቹ በማድረግ ምሳሌ የሚሆኑ ሥራዎችን እያከናወነች መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።