የሀገር ውስጥ ዜና

በኦሮሚያ ክልል የተተገበረው አዲስ አደረጃጃት ህዝቡ በቅርበት ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ ያስችላል ተባለ

By Meseret Awoke

September 04, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ተግባራዊ የተደረገው የቀበሌና ወረዳ አስተዳደር አደረጃጃት ህዝቡ በቅርበት ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ እንደሚያስችል ተገለጸ።

በክልል አዲስ የቀበሌና የወረዳ አስተዳደር አደረጃጀት ስራ ላይ መዋሉን በማስመልከት በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሃላፊው በመግለጫቸው፥ አደረጃጀቱ የአገልግሎት አሰጣጥን የማሻሻል፣ ሰላምን የማስፈንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በቅርበት የመፍታት ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፤ መዋቅሩ መንግስትና ህዝብን የሚያቀራርብ ትልቅ ውሳኔ ነው ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል መንግስት እና ፓርቲው የወረዳና የቀበሌ መዋቅርን በመከለስ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱ ምቹና ተደራሽ እንዲሆን በመስራት ላይ እንደሚገኙም ነው ያረገታገጡት፡፡

በአደረጃጀቱ ቀልጣፋና ምቹ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲኖር ብሎም የህዝቡ ችግር በጥናት እና በእውቀት መፍትሔ እንዲያገኝ የሚያስችል ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

ህዝቡ በልማት ተጠቃሚ እንዲሆንና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ህዝቡን ባሳተፈ ውይይት ምላሽ እንዲያገኙ ከማድረግ አኳያም አደረጃጀቱ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

የአደረጃጀቱ ተግባራዊ መደረግ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣም ትልቅ ዕድል ያለው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ለህዝቡ በቅርበት አገልግሎት እንዲሰጡም እውቀት ያላቸው፣ የህዝብ ተቆርቋሪነት የተላበሱና በስነ-ምግባር የተመሰገኑ መሪዎች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡ ከእነኚህ መሪዎች ጋር በቅርበት እንዲሰራም ጥሪ ማቅረባቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

ብልጽግና ፓርቲ የህዝቡን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲመለሱ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡