Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዘላቂ የክትመት ሽግግርን ለማሳካት ቁርጠኛ ናት – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዘላቂ የክትመት ሽግግርን ለማሳካት ቁርጠኛ ናት ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።

በአፍሪካ ከተሞች ፎረም የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካን እሳቤዎች እውን ለማድረግ ለረጅም ዘመን የተግባር ቁርጠኝነቷን አሳይታለች ብለዋል።

የነገ የአፍሪካ ክትመትን የተሻለ ለማድረግ የሚመክረውን ጉባዔ ኢትዮጵያ በማስተናገዷ ክብር እንደሚሰማት ጠቅሰው፥ የአፍሪካ ከተሞች ፎረም የአህጉራችንን ልማት ወደፊት ለማራመድ የጋራ ቁርጠኝነትን የምናሳይበት ነው ብለዋል።

ፎረሙ ስለ አፍሪካ ዕድገት ሀሳቦችን ለመለዋወጥ፣ ዘላቂ፣ አካታችና የበለጸጉ ከተሞች እንዲኖሩ በጋራ ለመሥራት ግብ የሚቀመጥበት ወሳኝ መድረክ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአጀንዳ 2063 የምንመኛትን የአፍሪካ ክትመት የመፍጠር ራዕይን ለማሳካትና ለችግሮች አህጉራዊ መፍትሔ ለመስጠት እንደሚያስችልም አንስተዋል።

አሁን እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ከተለመደው አካሄድ መውጣት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ከአህጉራዊ ግቦች አንፃር ተለዋዋጭ የፖለቲካ ስልትና ጠንካራ ውሳኔ ማሳለፍ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ አኩሪ ታሪክና ዕድሜ ጠገብ የዲፕሎማሲ ልምድ ያላት ከመሆኗ አኳያ የጋራ አህጉራዊ ምኞቶቻችንን በማሳካት ረገድ በፅናትና በቁርጠኝነት ስትሰራ መቆየቷን አንስተው፤ አሁንም የመሪነት ሚናዋን ታጠናክራለች ብለዋል።

በኢኮኖሚ ትስስር፣ በመሠረተ ልማት እድገትና በፖለቲካዊ አንድነት የተቀናጀ የአፍሪካ ክትመትን እውን ለማድረግ የዛሬው ፎረም ልዩ ዕድል እንደሆነ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አፍሪካ የከተማ ትራንስፎርሜሽን ላይ ትገኛለች ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከተሞቿ በፍጥነት እያደጉ መሆናቸው ዕድልም ፈተናም ይዞ መምጣቱን ጠቁመዋል።

በዚህ ፈጣን የከተሞች ዕድገት ውስጥ የኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገትንና የአካባቢን ዘላቂነት ለማጐልበት የከተሞቻችንን አቅም መጠቀም አለብን ብለዋል።

ከተሞች ውጤታማ በሆነ መንገድ ከተመሩ ትልቅ የልማት አቅም፣ የፈጠራ፣ የኢንዱስትሪና የሥራ ዕድል ፈጠራ ማዕከላት እንደሚሆኑም ጠቁመዋል።

የአፍሪካ ስኬት የሚወሰነው በጋራ ጥረት፣ ጥንካሬዎቻችንን በመጠቀምና የአጀንዳ 2063 መርሆዎች ቁርጠኛ በመሆን ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት የጋራ ግቦች ማዕቀፍ ውስጥ ዘላቂ አህጉራዊ ክትመትን ለማሳካት ቁርጠኛ እንደሆነችም አረጋግጠዋል።

Exit mobile version