Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የቻይናው ቶዮ ሶላር ኩባንያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቬትናም የሚገኘው የቻይናው ቶዮ ሶላር ኩባንያ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ስር በሚገኙ የኢንቨስትመንት ማዕከላት ውስጥ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ከቶዮ ሶላር ዋና ስራ አስኪያጅ ሊ ሁያንግን ጋር በነበራቸው ውይይት÷ በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና ስላለው የኢንቨስትመንት አማራጭና መሰረተ ልማት ገለፃ አድርገዋል፡፡

በተጨማሪም የተለያዩ የኢንቨስመንት ማበረታቻዎችን እንዲሁም በመንግስት በኩል የተደረጉ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በቀጣይም የቶዮ ሶላር ኩባንያ የቅድመ ኢንቨስትመንት ምልከታዉን አጠናቆ ወደ ስራ እንዲገባ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግም አረጋግጠዋል።

ሊ ሁያንግ በበኩላቸው÷ ኩባንያቸው ስለ ኢንቨስትመንት እቅዱ እንዲሁም ኩባንያው ያለበትን ወቅታዊ የስራ እንቅስቃሴና በመጀመሪያ ምዕራፍ ሊያከናውናቸው ባቀዷቸው ስራዎች ዙሪያ ገለፃ አድርገዋል፡፡

ኩባንያው ወደ ስራ ሲገባ በመጀመሪያው ምዕራፍ 5 ሄክታር የለማ መሬት ተረክቦ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው ወደ ስራ ሲገባም 100 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ኢንቨስት እንደሚያደርግ የተገለፀ ሲሆን ከ400 በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም በቋሚነት የስራ እድል ይፈጥራል ተብሏል።

መካከለኛው ምስራቅ፤ ህንድና አሜሪካ የኩባንያው ምርቶች መዳረሻ ገበያዎች እንደሚሆኑ መገለፁን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version