የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፈተና ውስጥ ሆኖም ፈጣን ዕድገት ማስመዝገቡ ተገለጸ

By Mikias Ayele

September 04, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ሥድስት ዓመታት በፈተና ውስጥ ሆኖም ከአፍሪካ ሀገራት ፈጣን ዕድገት ማስመዝገቡን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ገለፁ፡፡

የኢትዮ-ቻይና ከፍተኛ የቢዝነስ ፎረም በቤጂንግ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በዚህ ወቅት  ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር÷ ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ከምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ መሆኗን አስረድተዋል፡፡

ያላት የካፒታል ገበያ፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እና ሌሎች ሁኔታዎች ለኢንቨስትመንት ምቹ እንደሚያደርጋት ገልጸው÷ የግብርና ልማት፣ ቱሪዝም፣ የአምራች እና ሌሎች ዘርፎች አዋጭ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚን በመገንባት ሂደት ላይ መሆኗን በማስታወቅ ዘርፉ ለአልሚዎች ክፍት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በጤናው ዘርፍ ለመሰማራት የሚያስችሉ መሰረተ-ልማቶች የተሟሉ መሆናቸውን ያስታወቁት ደግሞ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ናቸው፡፡

በአፈወርቅ እያዩ