አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ያደረገቻቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ለአልሚዎች አዳዲስ ዕድሎች መክፈታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ አስገነዘቡ፡፡
በቤጂንግ እየተካሄደ በሚገኘው የኢትዮ-ቻይና ከፍተኛ የቢዝነስ ፎረም ላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር÷ ቻይና የምትከተለውን የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ኢትዮጵያ ታደንቃለች ብለዋል፡፡
የሁለቱን ሀገራት ስትራቴጂካዊ አጋርነት የበለጠ ለማጠናከር ኢትዮጵያ እንደምትሠራ አረጋግጠው÷ የምትገኝበት ቁልፍ ጂኦ-ፖለቲካዊ ሥፍራ ከማዕድን ሀብት እና ከአላት የሰው ሃብት አቅም ጋር ተደምሮ ተፈላጊቷን ከፍ እንደሚደርገው አብራርተዋል፡፡
በሁሉን አቀፍ ትብብር ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ለመሥራት ዝግጁ መሆኗን በመግለጽ÷ ቻይናውያን አልሚዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቀርበዋል፡፡
ከለዚህም የተለያዩ የፖሊሲ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን አስታውቀው ማሻሻያዎቹ ኢንቨስትመንትን የሚያበረታቱና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በአፈወርቅ እያዩ