አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከቻይና ኢኮኖሚና ንግድ ጉዳዮች አማካሪ ከሆኑት ሊው ጋር ተወያዩ።
በውይይታቸውም በቅርቡ ጎተራ አከባቢ ስለሚጀመረው ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ግንባታ ዙሪያ መክረዋል።
ጎተራ አከባቢ የሚካሄደው ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ግንባታ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የቻይናው ሲሲሲሲ በጋራ የሚያካሂዱት ነው።
በውይይታቸውም የመኖሪያ መንደሩ የዲዛይን ስራን ጨምሮ የግንባታ ፖሊሲ እና ሁለቱ አካላት በጋራ በሚሰሩባቸው ማዕቀፎች ዙሪያ ምክክር አድርገዋል።
በውይይቱ ወቅት የጎተራ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ግንባታ በቅርቡ በይፋ እንደሚጀመር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተናግረዋል።
ጎተራ አከባቢ የሚገነባው ይህ የመኖሪያ መንደር የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ የነበረበት ይዞታን ጨምሮ በጠቅላላው በ27 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ መሆኑን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ግንባታው በለገሃር ከሚገነባው ግዙፍ የመኖሪያ መንደር ግንባታ ቀጥሎ የከተማ አስተዳደሩ ሁለተኛው ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ግንባታ ፕሮጀክት እንደሆነ ይታወቃል።