አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2025 የሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመርያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ታንዛኒያን ይገጥማል፡፡
ጨዋታው ምሽት 1 ሠዓት ላይ በታንዛኒያ ዳሬ ሰላም ቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም ላይ ይደረጋል።
ዋልያዎቹ ትናንት በቤንጃሚን ምካፓ ናሽናል ስታዲየም የመጨረሻ ልምምዳቸውን ማድረጋቸውን የእግር ኳስ ፌደሬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡
በዛሬው ጨዋታም ኢትዮጵያ አረንጓዴ ማልያ፣ ቢጫ ቁምጣ እና ቀይ ካሶተኒ እንዲሁም ታንዛንያ ሰማያዊ መለያ የሚጠቀሙ ይሆናል።
ሴኔጋላዊያኑ ኢሳ ሲይ (ዋና)፣ ጂብሪል ካማራ (ረዳት)፣ ኖሀ ባንጎራ (ረዳት)፣ ኤልሀጂ አማዱ (አራተኛ) እና ደቡብ ሱዳናዊው ማኩር ማሲር በኮሚሽነርነት ጨዋታውን እንዲመሩም በካፍ ተመድበዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁለቱንም የ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመርያ ጨዋታዎች ታንዛኒያ ላይ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡
በዚሁ መሠረት የመጀመሪያውን ጨዋታ ዛሬ ከታንዛኒያ ሁለተኛውን ጨዋታ ከኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጋር ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም የሚያደርግ ይሆናል፡፡