Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሱዳን ቀውስ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ኢትዮጵያ የጀመረችው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሱዳን ቀውስ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ኢትዮጵያ የጀመረችው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች አመለከቱ፡፡

የሱዳን ቀውስ እና ቀጠናዊ ተፅእኖ፡ አንድምታ ለኢትዮጵያ! በሚል መሪ ሃሳብ የብሔራዊ መረጃና ደኀንነት አገልግሎት የአቅም ግንባታ ስልጠና ማዕከል የሆነዉ የብሔራዊ ደኀንነት ዩኒቨርሲቲ ከውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የምክክር መድረክ መካሄዱን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከዉ መረጃ አመልክቷል።

በውይይት መድረኩ ወቅታዊው የሱዳን ፖለቲካዊ ቀውስ ታሪካዊ ዳራ፣ መነሻ ምክንያቶችና ተዋናዮች፤ የሱዳን ግጭት በቀጣናው እና በኢትዮጵያ ላይ እያስከተለ ያለውና የሚያስከትለው ተጽዕኖ እንዲሁም የሱዳን ግጭት የወደፊት አዝማሚያ፣ የሰላም መፍትሄዎች እና ድህረ-ግጭት ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖራት ግንኙነት በሚሉ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ የተሰሩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደተደረገባቸው የአገልገሎት መስሪያ ቤቱ መረጃ ጠቁሟል።

መድረኩ በሱዳን የተቀሰቀሰው ቀውስ በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናዊያን ለስደት እንዲዳረጉ ምክንያት መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ ሱዳናዊያን ስደተኞችን ከተቀበሉ ሀገሮች አንዷ መሆኗን ያሳየው ጥናቱ ከዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ስደተኞቹ መሠረታዊ ፍላጎታቸው ተሟልቶላቸው እንዲኖሩ የኢትዮጵያ መንግስት የሚያደርገው እንቅስቃሴ የሀገራቱን የቆየ ወዳጅነትና የህዝቦችን አብሮነት የሚመጥን በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የመድረኩ ተሳታፊዎች መግለፃቸዉን መረጃዉ አመልክቷል፡፡

በሱዳን ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የግጭቱ ተጠቂዎች እንደሆኑ በመድረኩ የተመላከተ ሲሆን÷ ኢትዮጵያ ሁሉንም አካላት ተጠቃሚ በሚያደርገውና ሰላማዊ በሆነው መንገድ ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታ የጀመረችውን ጥረት የአፍሪካዊያን ችግሮች በራሳቸዉ በአፍሪካዊያን መፈታት አለበት የሚል አቋም ከሚያራምደዉ የአፍሪካ ህብረትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅንጅት ለመፍታት እያደረገች ያለችዉን እንቅስቃሴ አጠናክራ መቀጠል እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ያለው ጂኦ ፖለቲካዊና የደኅንነት ሁኔታ ተለዋዋጭ በመሆኑ የአካባቢው ሀገራት ያላቸውን የመልማት ዕድል አሟጠው ለመጠቀም እንቅፋት ሆኗል ያሉት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ ቀጣናው የራሱ ችግሮች ያሉበት ቢሆንም ከሩቅ እየመጡ የአፍሪካ ቀንድ ከብጥብጥና ግጭት እንዳይወጣ ለማድረግ የሚጥሩ አካላት መኖራቸው በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሆን አድርገዋል ነው ያሉት፡፡

ችግሩን በመረጃና በዕውቀት ላይ ተመስርቶ በዘላቂነት ለመፍታት ይህን መሰል ጥናቶችና ውይይቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል፡፡

የሱዳን ችግር ኢትዮጵያን በቀጥታ ተጎጂ የሚያደርግ ነው ያሉት አቶ ሲሳይ ኢትዮጵያ ለሱዳን ካላት ቀናኢ እሳቤ በተጨማሪ ለራሷም ጥቅምና ደኅንነት ስትል ችግሩን ሁለቱም ተፋላሚ ሀይሎች በሰላማዊ መንገድ እና በዉይይት እንዲፈቱት ትሠራለች ብለዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ በበኩላቸው÷ የአፍሪካ ቀንድ ውስብስ በሆኑ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁነቶች ውስጥ እያለፈ ነው ብለዋል፡፡

ከነዚህ ሁነቶች አንዱ የሱዳን ግጭት መሆኑን ያነሱት አቶ ጃፋር ግጭቱ በሱዳን ላይ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠባሳ እያሳረፈ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የጎረቤት ሀገራት ሰላም ኢትዮጵያ ለጀመረችው የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ጉዞ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን ያነሱት አቶ ጃፋር ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ በወንድመማማችነት መንፈስ የሚደረገው ድጋፍ የጎላ ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ታዜር ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸዉ÷ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን መሠረት አድርጋ ወደ ተጨባጭ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቷ ለታሪካዊ ጠላቶቿ የእግር እሳት ሆኖባቸዋል፡፡

በዚህ ዘርፍ የሚጠኑ ጥናቶችና የሚደረጉ ውይይቶች ለከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችና ለፖሊሲ አውጭዎች ተደራሽ ስለሚሆኑ ጠቀሜታቸው የላቀ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

የዉጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዲ ዘነበ÷ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሰሜንና ከማዕከላዊ የአፍሪካ ሀገራት ጋርም ጭምር የምትጎራበት ሰፊ የቆዳ ሽፋን ያላት በመሆኑ ኢትዮጵያ ለቀዉሱ ዘላቂ እልባት ለመስጠት ከእነዚህ ሀገራት መስራት እንደሚጠበቅባት አመልክተው በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች እያደረገች ያለችዉን ድጋፍ በሰላሙም ለመድገም ጥረቱን አጠናክራ መቀጠል አለባት ብለዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ከውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት፣ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከዲያስፖራ ኤጀንሲ፣ ከስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት እንዲሁም ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

Exit mobile version